ሰላምን መቼ ነው የምናቅደው?

10
🕊️
ጆን ጊቭሰን የተባሉ ጸሐፊ “የሰላም ጽንሰ-ሐሳብ” በተሰኘው መጽሐፋቸው የአልበርት አንስታይን ንግግር ጠቅሰው ሲጽፉ “ሰላም በኃይል ሊጠበቅ አይችልም፤ ሊገኝ የሚችለው በመረዳዳት ብቻ ነው” ይሉናል።
የባሩክ ስፒኖዛን ንግግር ጠቅሰው ሲጽፉ ደግሞ “ሰላም የጦርነት አለመኖር አይደለም፤ ሰላም በጎነት፣ የቸርነት ዝንባሌ፣ በራስ መተማመን ነው” ይላሉ።
ስለ ሰላም ያለ ምክንያት አላነሳንም። ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፤ ጥቁሩ ደመና ተገፎ ሰማዩ ሲጠራ፤ ምድር ለዓይን ማራኪ ስትኾን፤ አበቦች ሲፈነድቁ፤ ወንዞች ጎድለው የተነፋፈቁ ሲገናኙ፤ የዓውደ ዓመት ድባብ በየቤቱ ሲገለጥ ሁሉም በአዲሱ ዓመት አዲስ ዕቅድን ያወጣል።
ተማሪው በትምህርቱ ውጤታማ ለመኾን፤ ነጋዴው ነግዶ ለማትረፍ፤ ሥራ ያጣው ሥራ ለማግኘት፤ ትዳር ያልመሠረተው ትዳር ለመመሥረት፤ የተጋቡ ወልደው ለማቀፍ፤ ከፈጣሪያቸው የራቁ ወደ ፈጣሪያቸው ለመቅረብ እና ሌሎችንም በየዓመቱ ያቅዳሉ።
በዓመቱ ያቀደው የተሳካለት ሌላ እቅድ ሲያወጣ፤ ያልተሳካለት ደግሞ ከአጋጠሙት ፈተናዎች እና ውድቀቶች ትምህርትን በመቅሰም በአዲሱ ዓመት እንደገና ይወጥናል።
አብዛኞች ግን ትልቁን ነገር ከዕቅዳቸው ውስጥ ይረሱታል። ሰላምን አያቅዱም። ከዕቅድ ዝርዝር ውስጥም አይካተትም።
🕊️ መቼ ይኾን ሰላምን የምናቅደው?
በክረምት የዘራ በበጋ እንዲሰበስብ፤ በሰኔ ትምህርቱን ያጠናቀቀ በመስከረም እንዲጀምር፤ ሥራ ያላገኘ እንዲያገኝ፤ በንግድ የከሠረ በአዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ እና በታማኝነት መንገድ ትርፋማ እንዲኾን፤ ትዳር ያላገኘ እንዲያገኝ፤ ከትውልድ ቀዬው የራቀ ወደ ቀዬው እንዲመለስ ሰላም አስፈላጊው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዓመትን ተከትሎ የሚታቀዱ ዕቅዶች እንዲፈጸሙ ሰላምን ማቀድ ይገባል። ከነጻነት በኋላ የመጀመሪያው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ጃዋሃርላል ኔህሩ “ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም፤ በነፍስ እርጋታ የሚመጣ ነው፤ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ሰላማዊ ለኾኑ ሕዝቦች ብቻ ነው” በማለት ሕዝብ ሰላማዊ እንዲኾን ይመክራሉ።
ያ ማለት ደግሞ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ሰላምን ማጽናት ከራሱ መጀመር፤ ሰላምን መፍጠር ይገባዋል ማለት ነው።
🕊️ሰላምን ባለማቀዳችን ምን አጣን?
ሰላምን አለማቀድ ግጭት እንዲሰፋ፤ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዲደርስ፤ ንጹሐን የሕይወት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ፤ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ፤ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት እንዲፈጠር፤ በነጻነት መንቀሳቀስ ቅንጦት እንዲኾን፤ እናቶች በሕክምና እጦት እንዲሞቱ፤ ሴቶች የጥቃት ሰለባ እንዲኾኑ አድርጓል። ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳትን አስከትሏል።
ምን ያክል መራራ ዋጋ ሲያስከፍል ነው ሰላም የሚታቀደው? ስንቶች የማይተካ ሕይወታቸውን ሲገብሩ፤ አካላቸውን ሲያጡ ነው ሰላም የሚታቀደው? ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል።
🕊️ ሰላምን እንዴት እናቅድ ?
“ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት ተከተላትም” ተብሎ እንደተጻፈ ሰላምን ማስቀደም፣ ሰላምን መከተል እና መጠበቅ ይገባል።
የአካባቢን ሰላም በማጽናት፤ ግጭትን ተከትለው ለጥፋት የተሰለፉ ኃይሎችን ወደ ሰላም ማቅረብ፤ የውይይት፣ የምክክር ባሕልን በሰዎች መካከል መገንባት፤ ማኅበራዊ የግጭት መፍቻ የሽምግልና ሥርዓትን ማጠናከር፤ ወጣቶች፣ ሕጻናት የሰላምን ጥቅም እንዲረዱ በማድረግ ሰላምን አቅዶ መፈጸም በየዓመቱ ያስፈልጋል።
ያለ ሰላም የአዲስ ዓመት ተስፋ እና ዕቅድ ስኬታማ አይኾኑምና ሰላምን ማስቀደም የስኬት በር ነው።
ካለፈ ትናንት የሚመጣ ነገ ይሻላል፤ ከሚመጣ ነገ ደግሞ ዛሬ ይበልጣል፤ የዛሬ ኃይሉ እና ጉልበቱ ደግሞ አሁን ላይ ነው። ለመጭው አዲስ ዓመት ሰላምን ማቀድ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለምና አሁን ማቀድ የጀግኖች ተግባር ነው።
ለአዲስ ዓመት” ሰላምን” ለማቀድ እርስዎ ምን አስበዋል 💬
ሃሳብዎን ያጋሩን።
#አሚኮ#ሰላምን_ማቀድ#ኢትዮጵያ
🇪🇹
#ባሕር_ዳር#ነሐሴ_20_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎች ከቁጥጥር ውጭ መኾን ምን ሥጋት ያመጣል?
Next articleየሰላም አማራጭን መጠቀም ለሕዝብ ሰላም መቆም ነው።