
የምዕራብ ጎጃም ዞን ”የውጫዊ ወረራ ስጋትን እና የውስጣዊ ጽንፈኝነት አደጋን በመቀልበስ ዘላቂ ሰላምን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልዕክት ከዞኑ ጠቅላላ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ከውስጥ እና ከውጭ ያሉ የተለያዩ ኀይሎች ጥምረት በመፍጠር ሙከራዎችን እያካሄዱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ይህን አደጋ ለመቀልበስ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች የድርሻቸውን መውጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የሚስተዋሉ የጸጥታ ስጋቶችን ለመቀልበስ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን አጥብቆ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች የውስጥ እና የውጭ ኀይሎች ጥምረት ሀገርን ለሌላ እልቂት እና ውድመት የሚዳርግ መኾኑን አንስተዋል።
በተደጋጋሚ የተደረጉ ሥልጣንን በኀይል የመያዝ ሙከራዎች ከመፍትሔ ይልቅ ለሁለንተናዊ ምስቅልቅል የዳረጉ ናቸውም ብለዋል። ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ለማድረግ አሁንም የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ከሰላም ግንባታ ሥራው ባሻገር የመንግሥት ሠራተኞች የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
