
በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ 1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በሶላት እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በታላቁ ዑመር መስጊድ እየተከበረ ነው።
የበዓሉ ተሳታፊዎች የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመወለዳቸውን ደስታ እና ክብር ለመግጽ በጋራ እያከበሩ እንደሚገኙ ነግረውናል።
በዓሉም የደግነት እና የደስታ መኾኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ለሌለው በማካፈል እና በመጠየቅ በአብሮነት የሚከበር በዓል መኾኑንም አንስተዋል።
ለሀገር ሰላም ዱዓ በማድረግ በአንድ ላይ ኾነው እያከበሩት መኾናቸውን ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተወካይ ሠብሣቢ ሶፊያና አሊ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አዛኝ እና ሩህሩህ ስለኾኑ ሕዝበ ሙስሊሙም በዕዝነት እና የሌላቸውን በመጠየቅ በዓሉን ማክበር አለበት ብለዋል።
በዓሉ የመወለዳቸው ደስታ እና መገለጫ መኾኑን ነው የገለጹት።
በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እና ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ምክር ቤቱ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድነት የአካባቢውን ሰላም እየጠበቀ እና ለሀገር ሰላም ዱዓ እያደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ጋሻው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
