
የኡም አይመን የመጀመሪያ ሙሉ ስማቸውም በረካ ቢንት ሳዕላባ አል ሀበሺ ነው። ከሀበሻ የሚወለዱ ሀበሻዊት (ኢትዮጵያዊት) ሴት ናቸው።
ኡም አይመን (የአይመን እናት) የሚለው መጠሪያ የተሰጣቸው አይመን የተባለውን የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ልጃቸውን ምክንያት በማድረግ የወጣላቸው ስም እንደኾነ ይነገራል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አማካሪ ሼህ ጀውሐር መሐመድ እንደገለጹት ኡም አይመን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደ እናት ኾነው እየተንከባከቡ ያሳደጉ ኢትዮጵያዊት ሴት ናቸው ብለዋል።
የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አባት በሕይወት በነበሩበት ወቅት ኡም አይመን ከኢትዮጵያ ምድር ወደ መካ ሄደው ለአባታቸው እና
ለቤተሰቦቻቸው አገልጋይ ኾነው እንደቆዩ ሼህ ጀውሐር አስረድተዋል። በኋላ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወላጅ እናት ሲሞቱ ሞግዚት ኾነው ልክ እንደ እናት አሳድገዋቸዋል።

ኡም አይመንም ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አቅፈው እና ተንከባክበው እንደ ልጃቸው ፍቅር ሰጥተዋቸዋል። የእናትነት ፍቅርን ለግሰው፤ አገልጋይ ኾነው ለነብያቸው ታምነዋል። የሃይማኖታቸውን ፍሬም በሕይወታቸው በተግባር ያሳዩ እናት መኾናቸውን ነው ያብራሩት።
ኡም አይመን ኢትዮጵያዊት መኾናቸው እስልምና እና ኢትዮጵያ ያላቸውን ትስስር የሚያጎላ እና ለነብዩ መሐመድ እድገት የኢትዮጵያውያን እናቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበር የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
