
1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል እየተከበረ ነው።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አማካሪ ሼህ ጀውሐር መሐመድ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በስብዕናቸው የተመሰገኑ እና በድንቅ የመሪነት ጥበባቸውም የታወቁ እንደነበሩ ተናግረዋል። በዓሉ ከልደታቸው ባሻገር የእስልምናን ብርሃን ለሙስሊሙ ያስተላለፉበትን ተልዕኮ፣ የቁርዓንን መውረድ እና አጠቃላይ የፈጣሪን ጸጋ የምናስብበት ነው ብለዋል።
የዚህ ታላቅ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ ስኬት መሠረቱ ደግሞ ነብዩ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በሕዝቡ ዘንድ “መሐመል አሚን” (ታማኙ) ተብለው እስኪጠሩ ድረስ ያካበቱት ወደር የለሽ እውነተኛነት እና የላቀ ሥነ ምግባር እንደኾነ ገልጸዋል። ይህ ስብዕናቸው በ40 ዓመታቸው የነቢይነትን አደራ ሲቀበሉ ማኅበረሰቡ መልዕክታቸውን በልቡ እንዲያሰርጽ እና በሃይማኖቱ እንዲጸና ትልቁን ድልድይ ፈጥሯል ነው ያሉት።
የነብዩ የመሪነት ጥበብ ከሥልጣን ማማ ላይ ኾኖ በማዘዝ ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ከሕዝብ ጋር በመዋሃድ እና ራስን በማዋረድ የታነጸ ነው እንጂ ይላሉ። የጦር አዛዥ፣ የመስጊድ ኢማም እና የቤተሰብ መሪ ኾነው ሳለ እንግዳ ሰው መጥቶ “ሙሐመድ ማን ነው?” ብሎ እስኪጠይቅ ድረስ ከሌላው የተለየ ማረፊያ አልነበራቸውም ብለዋል። ይህ የትህትና ልዕልና በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ሕያው ነበር ነው ያሉት።
ነብዩ በቤታቸውም ውስጥ ቢኾን ባለቤታቸው ዓኢሻ (ረ.ዓ) እንደመሰከሩት ሊጥ ሲያቦኩ ቤቱን በመጥረግ፤ ከጓደኞቻቸው ጋር ሲጓዙ በአንድ የጋማ ከብት ላይ አብረው በመፈናጠጥ የአገልጋይነትን ትክክለኛ ትርጉም በተግባር አስመስክረዋል ብለዋል።
ከነብዩ ታሪካዊ ክስተቶች መረዳት የሚቻለው ዋነኛው የመሪነት ጥበባቸው በዕዝነት፣ በእኩልነት እና በፍትሕ ላይ የተገነባ መኾኑን አንስተዋል።
ለሰው ልጅ ነፍስ ደኅንነት አጥብቀው ከመጨነቃቸው የተነሳ ሰዎች የእውነትን መንገድ ሲያስተባብሉ እጅግ ያዝኑ ነበር፤ ለዚህም ነው ቁርዓን “ሰዎች አላመኑም ብለህ ራስህን አታሰቃይ” በማለት ያጽናናቸው ይላሉ።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አዛኝ ከመኾንም ባሻገር የሰውን ልጅ ያለ አድልዎ ማቀፍን አስተምረዋል። “በቀዩ እና በጥቁሩ፣ በሀብታሙ እና በድሀው መካከል ከአላህ ፍራቻ (ተቅዋ) ውጭ ምንም ልዩነት የለም” በማለት የእኩልነትን ጽኑ መሠረት ጥለዋል ነው ያሉት።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሰላም እና የሰብዓዊነት እሳቤ የጦርነት ደመና ባንዣበበበት ወቅትም ቢኾን የፍትሕን ከፍታ በተግባር አሳይተዋል ብለዋል። ዛሬ ሀገራችንም ኾነ ዓለም ከተዘፈቁበት ውስብስብ ቀውስ ለመውጣት እነዚህ የሰላም፣ የይቅርታ እና አብሮ የመኖር ትምህርቶች ጊዜ የማይሽራቸው ፍቱን መድኃኒቶች እንደሚኾኑ ገልጸዋል።
የነብዩን ታላቅ አርዓያነት በእውነተኛው መንገድ መከተልን ማረጋገጥ የሚቻለው መላው ማኅበረሰብ የተሳተፈበትን ደስታ በመፍጠር እንደኾነ ሼህ ጀውሐር ጠቁመዋል። የሃይማኖቱ ተከታዮች የመውሊድን በዓል ሲያከብሩ ከዕለቱ ድግስ እና ዱዓ ባሻገር የነብዩን ርህራሄ በተግባር ማዋል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ምስኪኖችን፣ ወላጆቻቸውን ያጡ፣ አቅመ ደካሞችን እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በማሰብ ማዕድ ማካፈል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
