ጀማ ንጉሥ – የሐበሻው የመውሊድ መነሻ እና የዓሊሞች ማዕከል

7

 

በደቡብ ወሎ ምድር ታሪክ እና መንፈሳዊነት በተሳሰሩበት ታላቁ የጀማ ንጉሥ መስጂድ ውስጥ የመንፈሳዊ ደስታ እና የሃይማኖት ማዕበል ይንጸባረቃል።

ይህ ቅዱስ ስፍራ በሐበሻ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ በደመቀ ሁኔታ መከበር የጀመረበት የታሪክ እና የዕውቀት መገኛ ነው።

የበርካታ ዓሊሞች (ቁርዓን፣ ሐዲስ እና የሸሪዓ ሕጎች ዕውቀት ያላቸው የእስልምና ሊቃውንት) ማዕከልም ነው።

ከደሴ ከተማ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአልብኮ ወረዳ ርእሰ ከተማ ሳልመኔ በስተደቡብ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የጀማ ንጉሥ ኸሊፋ (ምትክ፣ አሥተዳዳሪ፣ ጠባቂ) መሐመድ ሷሊህ ዘመናትን የተሻገረው የጀማ ንጉሥ ታሪክ በመስራቹ በታላቁ አሊም ሐጅ ሰይድ ሙጃሂድ (ሼህ መሐመድ ሻፊ) ስም ይበልጥ እንደሚጎላ ነግረውናል።

መሥራቹ ይህንን ማዕከል ያቋቋሙት በጊዜው የነበሩ የኡለማዎች ስብስብ በሥርዓት ተሰባስበው ዕውቀት እንዲለዋወጡ፣ ማኅበራዊ ችግሮችን የሚፈቱበትን መድረክ እንዲፈጥሩ እና አስተምህሮውን በጥንካሬ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ በማሰብ እንደነበርም ገልጸዋል።

በጀማ ንጉሥ የመውሊድ በዓል ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚከበርም ጠቅሰዋል። አከባበሩ ከበዓሉ ሁለት ቀን ቀድሞ ይጀምራል ነው ያሉት። በዓሉ የሚጀምርበት የመጀመሪያው ቀን (ራምሳ) የበዓሉ መክፈቻ፣ መንፈሳዊ ዱዓዎች እና ዚክሮች የሚጀመሩበት ምሽት እንደኾነም አንስተዋል።

የበዓሉ ሁለተኛ ቀን (አወል) ደግሞ በዓመተ ሂጅራ አቆጣጠር ዋናው የነብዩ ልደት የሚከበርበት ታላቁ ቀን ነው ብለዋል። በዕለቱ ከማታ ጀምሮ መንዙማዎች፣ ሀድራ የተባሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች፣ የሀገር ሰላም እና ፍቅር መማማሪያ መድረኮች የሚካሄድበት እንደኾነም ጠቅሰዋል። የበዓሉ ሦስተኛው ቀን (ኸትሚያ) ደግሞ ታላቁ የመንፈሳዊ ስብስብ መደምደሚያ እና የጸሎት ማጠቃለያ ነው ብለዋል።

በእነዚህ ቀናት የመስጂዱ ግቢ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚሠባሠቡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ጸሎት ስፍራ ብቻ አይደለም። የጀማ ንጉስ ኸሊፋ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቦታው የሚሄዱ ነጋዴዎች አልባሳትን፣ ምግቦችን እና ሃይማኖታዊ ቁሳቁሶችን የሚያቀርቡበት ደማቅ ባሕላዊ ባዛር እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መገናኛ ማዕከል ጭምር እንደኾነም ገልጸውልናል።

ዘንድሮም በዓሉ የቀደመ ሥርዓቱን ጠብቆ መከናወን ጀምሯል ብለዋል። ታሪካዊውን እና መንፈሳዊውን በዓል በሰላም እና በደስታ ለማክበር ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አንስተዋል።

በመስጂዱ ውስጥ የቆዩ ቅርሶች እና ታሪካዊ ሀብቶች በጥንቃቄ ተጠብቀው ይገኛሉ ነው ያሉት። በመስጂዱ
በሸሆቹ እጅ በጊዜው የተጻፉ ጥንታዊ የኪታብ፣ የእጅ ጽሑፎች፣ የቆዩ የመስባሃ (የዚክር) ቅርሶች እንደሚገኙ ገልጸውልናል። ታሪካዊው መስጂድ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ባሻገር የበለጠ የጎብኝዎች መዳረሻ እንዲኾን ዘላቂ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልገው አንስተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አስያ ኢሳ የዘንድሮውን የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በዞኑ እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎች መዳረሻ ለኾነው ጀማ ንጉስ መስጂድ ነባሩን መንገድ የመጠገን እና የመጠጥ ውኃ ችግርን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

ለዚህም ከሃይማኖቱ ተከታዮች እና ከመንግሥታዊ ተቋማት ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት።

#አሚኮ #ቱሪዝም #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_19_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleመውሊድ – ከደስታ ባሻገር ምን?