እንኳን ለ1501ኛው የነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) የመውሊድ በዓል አደረሳችሁ

15
የነቢዩ መሐመድ ታሪክ ትውልድን ለበጎ ከሚቀርጹ ታሪኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ የተጠሩበትን ዓላማ ማክበር፤ ለተጠሩበት ዓላማ ዋጋ መክፈል፤ የተጠሩበትን ለሌሎች ማካፈል፤ የተጠሩበትን አክብሮ መኖር – እነዚህ ሁሉ ሺ መጻሕፍት የሚወጧቸው ትምህርቶች ናቸው፡፡
ነቢዩ የተጠሩበትን ዓላማ በሚገባ ስለተገነዘቡ አክብረው ኖረዋል፡፡ የተጠሩት ለተራና ርካሽ ነገር እንዳልሆነ ተገንዝበዋል፡፡
የተጠሩት ትውልድን ለመቅረጽና ታሪክን ለመቀየር መሆኑን አምነዋል፡፡ ያንንም በቃላቸው፣ በሥራቸውና በኑሯቸው አክብረውት ነኖረዋል፡፡
ለታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ተጠርተናል ብለን የምናምን ከሆነ ይህ የነቢዩ ሕይወት ታላቅ ትምህርት ይሆነናል፡፡ የተጠራንበትን ዓላማ በንግግራችን፣ በሥራችንና በሕይወታችን እንግለጠው፡፡
ነቢዩ ለተጠሩበት ዓላማ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ከቦታቸው ተሰደዋል፤ ምግብና መጠለያ ተነፍገዋል፤ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተዋል፡፡ ለሞት በሚያበቁ ፈተናዎች ውስጥ አልፈዋል፡፡ ጦርነት ተከፍቶባቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በአላህ ኃይል አሸንፈዋል፡፡ ክብር ያለ መከራ አይገኝምና፡፡ እውነተኛ ሰው ለዓላማው እንደ ነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ)ዋጋ ይከፍላል፡፡ ዓላማው የሚያስገኘውን ክብርና ጥቅም ብቻ ሳይሆን ዓላማው የሚያስከፍለውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ይሆናል፡፡
ነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) ከአላህ የደረሳቸውን መልእክት ለራሳቸው ብቻ አላስቀሩም፡፡ የተጠሩበትን ለሌሎች ለማካፈል ተግተዋል፡፡ መጀመሪያ በጣት ለሚቆጠሩ ሰዎች፣ በኋላም ለቅርብ ሱሐባዎች፣ በመጨረሻም ለዓለም መልእክቱን አዳርሰዋል ፡፡ እሳቸው የዘሩት ዘር እያፈራና እየጎመራ ተጉዟል፡፡ ዓላማችንን እኛ ማወቃችንና ማመናችን ብቻ ጥቅም የለውም፡፡ ሌሎች እንዲያውቁና እንዲያምኑ ልክ እንደነቢዩ ተገትተን መድከም አለብን፡፡
የነቢዩን መውሊድ ስናከብር ከሕይወታቸው እየተማርን፤ የተማርነውንም ለሀገረ መንግሥት ግንባታችን እየተጠቀምን እንዲሆን አደራ እላለሁ፡፡
በድጋሚ መልካም የመውሊድ በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ነሐሴ 19 ቀን 2018 ዓ.ም
Previous articleበብሔረሰብ አሥተዳደሩ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሠብሥቧል።
Next article“መውሊድ ታላላቆቻችንን የምናስብበት፣ መተባበር እና አብሮነት በተግባር የሚገለጽበት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ