
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከአገልግሎት ገቢ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ ታቅዶ እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተሠብስቧል። ይህም የዕቅዱን 87 ነጥብ 8 በመቶ መፈጸም ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ የተሠበሠበው ገቢ ከባለፈው ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያም የበጀት ዓመቱን ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ፈጠነ ጥላሁን የ2018 በጀት ዓመት የገቢ አሠባሠብ የአመራር አጀንዳ ኾኖ በየዕለቱ በትኩረት በመመራቱ የተሻለ መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በተዋረድ ያሉ የገቢ ሠብሣቢ ተቋማት ባለሙያዎች እና መሪዎች የገቢ አማራጮችን በማስፋት የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ ያሳዩት ተነሳሽነት የሚበረታታ እንደነበርም አንስተዋል።
የደረሰኝ አጠቃቀም ክትትል፣ የከተማ አገልግሎት ገቢ እና የአከራይ ተከራይ ገቢ በሚፈለገው ልክ አለመኾን በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉ ጉድለቶች ናቸው ያሉት ኀላፊው ችግሮቹ ወደ ቀጣይ ዓመት እንዳይሻገሩ እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እውን የሚኾኑት በሚሠበሠበው ገቢ ልክ መኾኑን ተናግረዋል።
በመሪዎች ቁርጠኝነት፣ በገቢ ሠብሣቢ ተቋሙ ጥብቅ ክትትል እና ለፀጋ ልየታ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በዚህ ዓመት የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ ተችሏልም ነው ያሉት።
ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከዚህ በላይ ገቢ ለመሠብሠብ የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳለው የጠቆሙት ዋና አሥተዳዳሪው ይህንን አቅም አሟጦ በመሠብሠብ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
