
የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና የቡሔ ክብረ በዓላት የሕዝቦች የማንነት መገለጫ፤ የባሕል እሴቶች ኾነው በድምቀት እየተከበሩ ነው።
እነዚህ በዓላት በዋናነት ልጃገረዶች የሚሳተፉባቸው፤ ድንቅ የባሕል ትርዒት የሚቀርቡበት፤ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ክዋኔዎች የሚንጸባረቅባቸው የአደባባይ ሁነቶች ናቸው።
ስያሜያቸው እንደየአካባቢው ይለያይ እንጂ የሚያስተላልፉት መልዕክት፤ የመነሻ መሠረታቸው፤ የሚከበሩበት ወቅት እና በበዓሉ ወቅት የሚከናወኑት ባሕላዊ ክዋኔዎች ተያያዥነት ያላቸው ናቸው።
እነዚህ ክብረ በዓላት ልጃገረዶች በባሕል አልባሳት አሸብርቀው፤ በጌጣጌጥ ደምቀው፤ በወንዶች ወጣቶች ታጅበው እና በአባቶች ተመርቀው በአደባባይ ልዩ የትርኢታቸውን በግጥም፣ በዜማ እና በውዝዋዜ ይከውናሉ። በዚህም ሁነቶቹ የበርካታ ጎብኝዎች ዐይን ማረፊያ እየኾኑ መጥተዋል።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ እንደገለጹት በክልሉ የሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በድምቀት እየተከበሩ በመዝለቃቸው በሕዝቡ በኩል በየዓመቱ በናፍቆት የሚጠበቁ ኾነዋል።
የዘንድሮው የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ክብረ በዓላትም ከባሕል መገለጫነት ባለፈ ለቱሪስቶች አይነተኛ መዳረሻ መኾን እንደቻሉ አስታውቀዋል። እነዚህ ክብረ በዓላት በተከበሩባቸው አካባቢዎች በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ተገኝተው መታደማቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ክብረ በዓላት በድምቀት መከበር የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ አስችሏል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።
በየመዳረሻዎቹ ለበዓሉ አከባበር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት፣ የባለሙያ ድጋፍ እና ክትትል የማድረግ እንዲሁም ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚረዱ የማስተዋዎቅ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ቢሮ ኀላፊው አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
