
በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው ዋግሹም ጤና ሳይንስ እና ቢዝነስ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት የትምህርት ዘርፎች ያሠለጠናቸውን 272 የጤና ባለሙያዎች አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን ኮሌጁ በጤናው ዘርፍ ያለውን የሰው ሃብት ክፍተት ለመሸፈን ያደረገውን አስተዋጽኦ አድንቀው ተመራቂዎች ሕዝብን በቅንነት እንዲያገለግሉም አደራ ብለዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ ኢዮብ ዘውዴ ኮሌጁ ከተፈራ ኃይሉ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት ተመራቂዎቹ የተግባር ልምምድ እንዲሠሩ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በጤናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የጋራ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የኮሌጁ መሥራች እና ሥራ አሥኪያጅ አታክልት ካሣሁን ኮሌጁ ከተመሠረተበት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሦሥት ዓመታት በትጋት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከ1ሺህ በላይ ሠልጣኞችን በዲፕሎማ እና በዲግሪ መርሐ-ግብር ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በምረቃው ወቅት 3 ነጥብ 93 ውጤት በማምጣት የወርቅ ዋንጫ ተሸላሚ የኾነው ሠልጣኝ መለሰ ሙሉጌታ “ራሴን በማብቃት እና በትጋት በመማር ለውጤት በቅቻለሁ፤ በቀጣይም ይህን ውጤቴን በዲግሪ ደረጃ ለመድገም ተዘጋጅቻለሁ” ሲል ተናግሯል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች፣ የኮሌጁ ኀላፊዎች፣ ተመራቂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
