
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ በዓል የአንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) አደረሳችሁ።
መውሊድ ታላላቆቻችንን የምናስብበት፣ መተባበርና አብሮነት፣ መተዛዘንና መፈቃቀድ በተግባር የሚገለጽበት ነው። ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፣ ማኅበራዊ ትሥሥር የሚጠናከርበትና በአንድነት አብሮ የሚያሳልፉት ታላቅ በዓል ነው።
ይህን በዓል የምናከብረው የዓለሙ እዝነት፣ ለሠናዮች መልካሙን አብሣሪ፣ ለተከታዮቻቸው ሐላል እና ሐራሙን አስተማሪ የኾኑት ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮና መልካም ሥራ የሚታወስበት፣ የሚዘከሩበትና የሚወደሱበት በመኾኑ ነው።
የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ተግባራት ሳይደበዝዙ በድምቀት፣ ሳይሻሩ በሕያውነት ዛሬም ድረስ አሉ። ይህን በዓል በጋራ ስናከብር በተሟላ የመልካምነት ዕሴት፣ በፍቅር እና በአብሮነት፣ በሰላም፣ በመተሳሰብ፣ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት ሊኾን ይገባል።
ለቆምንለት በጎ ዓላማ መትጋትን፣ ለሌሎች የሚተርፍ መልካም ፍሬ መስጠትን፣ ሀገርና ሕዝብ የሚያወሱት ዐሻራን ማሳረፍ፣ በኅብረት መሥራት፣ በጽናት መቆም እና በዕውቀትና በትዕግሥት ወደ ግባችን መገሥገሥም ያስፈልጋል።
በድጋሜ እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) በሰላም አደረሳችሁ!
