ግዙፉን ስታዲየም ወደቀደመ ግርማው!

10
🏟️
የወልድያ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየምን ከደረሰበት ጉዳት ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ስታዲየሙን ነጻ በማድረግ ጥገና እንዲደረግለት ለክልሉ መንግሥት ርክክብ ማድረጉን አሚኮ ከወራት በፊት መዘገቡ የሚታወስ ነው።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት ለስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል። በዚህም የስፖርት መሠረተ ልማቶች በተሻለ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
በወልድያ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት ቁርጠኝነቱን ወስዶ ለስታዲየሙ ጥገና የሚውል አስፈላጊውን በጀት መመደቡን አስታውቀዋል። ከቀጣይ መስከረም 2019 ዓ.ም ጀምሮ ጨረታ በማውጣት የጥገና ሥራው እንደሚጀመርም ገልጸዋል።
ከጥገና ሥራው ጎን ለጎን በከተማዋ ተጨዋቾችን እና የስፖርት ቤተሰቡን ማስተናገድ የሚችሉ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲሟሉ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች እና ሌሎችም የአገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ይህንን መሠረት አድርገው ወደ ሥራ የገቡ ባለሃብቶች መኖራቸውንም ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል። ሌሎች ባለሃብቶችም በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲያለሙ ጥሪ የማድረግ እና ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“መውሊድ ታላላቆቻችንን የምናስብበት፣ መተባበር እና አብሮነት በተግባር የሚገለጽበት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ