ግንድ እና ወርቅ ይዞ ከመዞር የታቀበው ወንዝ ዛሬስ?

8
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መፍለቂያ እናት ናት። ከኢትዮጵያ መሀል ሀገር ተነስቶ በርካታ የሀገሪቱን አካባቢዎች በማቆራረጥ ከሀገር የሚወጣው ታላቁ ወንዝ ጉዞው ብቻውን አልነበረም። ከአፈር እስከ ወርቅ የኢትዮጵያን ውድ ሃብቶች ተሸክሞ ነበር የሚነጉደው።
ታዲያ ኢትዮጵያ ወንዙ ከጉያዋ ፈልቆ ሲፈስስ ለዘመናት በትዝብት እና በቁጭት ከመመልከት ውጭ ከኤሌኬትሪክ ኀይል እስከ ዓሣ ምርት ለአገልግሎት ተጠቅማበት አታውቅም።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅማ ዕድገቷን ማረጋገጥ እንዳትችል ግብጽን ጨምሮ ሌሌሎች ጠላቶቿ በብዙ ሴራዎች አስረዋት ኖረዋል። ታዲያ የውኃ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም አለመቻሏ በድህነት እና በጉስቁልና ለመኖሯ እንደ አንድ ሰበብ ተደርጎ ይጠቀሳል።
ግብጽ የዓባይ ወንዝን ተከትላ የገነባቻቸው ትላልቅ ግድቦች በግብርና ዘርፍ ዋነኛ የምግብ ዋስትና ምንጭ፤ ለብዙ ሺህዎች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና የኢኮኖሚ የደም ሥር ኾነው ለዘመናት አገልግለዋታል። በዚህ ረገድ የአሰዋን ግድቡ ናስር ሐይቅ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ከሐይቁ በዓመት ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ ቶን የዓሣ ምርት እንደምታገኝ እና ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች በዓሣ ማስገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መኾናቸውን የግብጽ ብሔራዊ ዲጅታል ቤተ መጽሐፍት ድረ ገጽ ላይ የሰፈሩ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዛሬ ላይ የግብጽ በብቸኝነት ዓባይን የመጠቀም የዘመናት ሴራ አብቅቷል። ዓባይ ለእናት ሀገሩ ሲሳይ የሚኾንበት የታሪክ ምዕራፍ ተጀምሯል።
በኢትዮጵያ ምድር የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይኾን ለሀገሪቱ አዲስ የኢኮኖሚ ተስፋን የሰነቀ የውኃ ኢኮኖሚ ማዕከል እየኾነ መጥቷል።
ግድቡ የያዘው ግዙፍ ሰው ሠራሽ የንጋት ሐይቅ አሁን ላይ ለሀገሪቱ እምቅ የዓሣ ሀብት ልማት በር መክፈቱ ነው የተነገረው።
🐟 የንጋት ሀይቅ እና የወጣቶች ተጠቃሚነት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በአሁኑ ወቅት በዓሣ ሀብት ልማት ረገድ ትልቅ እንቅስቃሴ እያስተናገደ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሐይቁ ውስጥ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳሩን የጠበቁ እና ለገበያ ተፈላጊ የኾኑ በርካታ የዓሳ ዝርያዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተራቡ ይገኛሉ። በግድቡ ዙሪያ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት እየተደራጁ በዓሣ ልማት በሰፊው መጠቀም ጀምረዋል። ጅምሩ ለአካባቢው ወጣቶች አዲስ እና አስተማማኝ የገቢ ምንጭ መፍጠርም ችሏል።
📈 ሕዳሴ ከኃይል ማመንጫነት ወደ ምግብ ዋስትና ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የኢንዱስትሪ ክፍተቱን ለመሙላት ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን በንጋት ሐይቅ ላይ የዓሣ ሀብት ልማትን በመተግበር የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መረጃ እንደሚያሳየው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከንጋት ሐይቅ ብቻ 1ዐ ሺህ 799 ቶን ዓሳ ማምረት መቻሉ ገልጿል።
የዓሣ ሀብት ልማት ባለሙያዎች እንደሚሉትም ከሕዳሴው ግድብ ንጋት ሐይቅ የሚገኘው የዓሣ ምርት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ምርትን በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት ታስቦ እየተሠራበት ይገኛል።
🌟 የሕዳሴው ግድብ ራዕይ አሁን ላይ ሕዳሴ ግድብን ተከትሎ እየተከናወኑ የሚገኙት ሥራዎች በሙሉ ጅምሮች ናቸው። በቀጣይ ዓመታት በኹሉም ዘርፎች ያለው እምቅ አቅም ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ያስችላታል። በፀጋዋ ልክ ለልማት የጀመረችውን ውጥን በመደገፍም የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ትልቅ አሻራ እንደሚያሳርፍ ታምኖበታል።
አልፎም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ የተጀመረው የዓሣ ልማት ፕሮጀክት በአፍሪካ ትልቁ የዓሣ ምርት ማዕከል ለማድረግ በሰፊው እየተሠራበት እንደሚገኝ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዲጂታል ቴክኖሎጂ ለታዳጊዎች ዕድል ወይስ?
Next articleየኢትዮጵያ ከተሞችን መልክ የገለጠው የኮሪደር ልማት