
በደቡብ ጎንደር ዞን በተካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ51 ሺህ በላይ ዜጎች በማዕድ ማጋራት ተጠቃሚ ኾነዋል። “ለአንድ ተማሪ አንድ ደርዘን ደብተር” በሚል መሪ መልዕክትም ከ54 ሺህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ አንጓች ፋሲካው እንደገለጹት ይህ ስኬት በዞኑ በሚገኙ መምሪያዎች እና ተጠሪ ጽሕፈት ቤቶች የጋራ ርብርብ የተገኘ ነው። የበጎ ፈቃድ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተው ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ቀድሞ መድረስ ለትውልድ የሚተርፍ ተግባር መኾኑን ጠቅሰዋል።
የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎችም በደም ልገሳ እና በቤት እድሳት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የጠቆሙት።
በተደረገው ድጋፍ ከተጠቀሙ ወገኖች መካከል የሦሥት ልጆች እናት ወይዘሮ ደማም ተሾመ የተደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ልጆቻቸውን ከጎዳና ሕይወት ታድጎ በነጻነት እንዲማሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
የ7ኛ ክፍል ተማሪዋ ዳሳሽ ምሥጋናው የተደረገላት ድጋፍ ከጓደኞቿ ጋር እኩል እንድትሰለፍ የሞራል ስንቅ እንደኾናት እና ጠንክራ በመማር ዶክተር የመኾን ራዕይ እንድትሰንቅ እንዳስቻላት ተናግራለች።
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
