
የደብረ ብርሃን ከተማን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት የሚያጠናክር እና በክልሉ መንግሥት ከ275 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበለት የደረቅ ጭነት ተርሚናል ግንባታ በይፋ ተጀምሯል።
1 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው እና በክልሉ የመጀመሪያ የኾነው ይህ ፕሮጀክት ሙሉ የግንባታ ሥራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተገልጿል።
ተርሚናሉ ሥራ ሲጀምር በቀን እስከ አንድ ሺህ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
የክልሉ መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ የከተማዋን የኢንዱስትሪ እና የንግድ እንቅስቃሴ የሚያግዝ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ለቀጣይ ማስፋፊያዎችም ከተማ አሥተዳደሩ፣ ባለሀብቶች እና ማኅበረሰቡ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የግንባታው መጀመር የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰ መኾኑን ገልጸዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት እና በወቅቱ እንዲጠናቀቅ በቅርበት የማገዝ ኀላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
