የሦስት ዓመታት የተማሪና ትምህርት ቤቶች ናፍቆት ሊፈታ ይኾን?

7
ላለፉት ሦሥት ዓመታት ተማሪዎችን የተራቡት ትምህርት ቤቶች ከናፈቋቸው ተማሪዎች ጋር ሊገናኙ እነሆ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
የጸጥታ ችግር ያለያያቸው የዕውቀት መገብያ ትምህርት ቤቶች ከተማሪዎቻቸው ውጭ ምንም ናቸው። አሁን ላይ ተማሪዎቻቸውን በጉያቸው ሊያቅፉ ናፍቀዋል። ግጭት ይብቃ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው በነጻነት ይቦርቁ፤ ዕውቀትም ይገበያዩ እያሉም ይገኛሉ።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም የናፈቋቸውን 476 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው ዕውቀት ይገበያዩ ዘንድ አቅደው እየተንቀሳቀሱ ነው።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታው አለሙ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለማስተማር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ሰኔ መጨረሻዎቹ ላይ ከታችኛው የትምህርት መዋቅር ጋር በጋራ ውይይት ተደርጎ ሲሠራ ስለመቆየቱም ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ በተፈጠረ የሰላም እጦት ችግር ተዘግተው የነበሩ በርካታ ትምህርት ቤቶችን በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሥራ እንዲጀምሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሌሎች አካላት ጋር ሰፋፊ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ብለዋል ኀላፊው።
ተዘግተው ከነበሩት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተደረገው ውይይት እና መግባባት በክረምት ወቅት ሥራዎችን ሲሠሩ እንደቆዩም ጠቅሰዋል።
ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካ ነጻ ቢኾንም ሰላም በማይፈልጉ አካላት የትምህርት ዘርፉ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ስለመቆየታቸው አስታውሰዋል።
በአሥተዳደሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የነበሩትን ጨምሮ ልዩልዩ ግብዓቶች እንዲሟሉላቸው በክረምት ወራት ሥራዎች ተሠርተዋልም ብለዋል።
በተለይም፦
👉 ትምህርት ቤቶችን ማጽዳት እና መጠገን
👉 ወንበሮችን እና ጠረጴዛዎችን ማሟላት
👉 ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችን መገንባት
👉 ችግኞችን በመትከል ግቢያቸውን ማሳመር
👉በበጋ ወራት ግንባታቸው የተጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ማጠናቀቅ እና
👉 በማጠናከሪያ ትምህርት ከ9ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስተማር መቻሉን ገልጸዋል። ለትምህርት ዘመኑ ሁሉም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ በንቅናቄ ምዝገባ ተጀምሯል ያሉት ኀላፊው በፓይለት ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች ምዝገባ ተጀምሮ ትምህርት ተወስዷል ነው ያሉት።
ዛሬ ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም ደግሞ በሁሉም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯልም ብለዋል። እስከ መስከረም 05/2019 ዓ.ም ድረስም ሁሉንም ተማሪዎች መዝግቦ ለማጠናቀቅ ታቅዷል ነው ያሉት።
ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ 476 ሺህ 588 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ስለመታቀዱም ነው አቶ ደስታው የገለጹት። መስከረም 05/2019 ዓ.ም ተማሪዎች እና መምህራን የሚገናኙበት ቀን ስለመኾኑም ገልጸዋል።
“የትምህርት ጉዳይ የማይመለከተው አካል የለም” ያሉት ኀላፊው የተማሪዎች ምዝገባ የተሳካ እንዲኾን እርብርብ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበ275 ሚሊዮን ብር ወጭ ለደብረብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ከፍታ!
Next articleበደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባው የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት ማዕከል ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ገባ።