
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የ2018 ዓ.ም የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ፣ የሰላም እና የአብሮነት መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱም ለክልላችን እና ለሀገራችን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብሏል።
የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልደት ለሕዝብ ሙስሊሙ ብቻ ሳይኾን ለሰው ልጅ ሁሉ የሩህሩህነት፣ የመቻቻል እና የፍቅር ትምህርት የተሰበከበት ታላቅ ክስተት ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባስተማሩት መለኮታዊ ቃል “ለዓለማት እዝነት እንጂ ሌላ አድርገን አልላክንህም” (ሱረቱል አንቢያ 107) እንደሚለው በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ለሰዎች ሰላም፣ ለፍትሕ እና ለሰብዓዊ ክብር የተጋደሉበት ነበር፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዘመን ጀምሮ ከእስልምና ጋር ያላት ጥልቅ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ትስስር በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ የታወቀ ነው ብሏል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ ባልደረቦች (ሶሓቦች) በመካ በነበረው መከራ እና ስደት ምክንያት ወደ ሐበሻ ምድር ሲመጡ የዚያን ጊዜው የሐበሻ ንጉሥ አርማህ (ነጃሺ) በፍትሕ እና በቅንነት ተቀብሎ የመጠለል መብታቸውን አስክብሯል፡፡ ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ሀገራችን ሲናገሩ “የእውነት ምድር እና ማንም የማይበደልባት የፍትሕ ሀገር ናት” በማለት አክብሮታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ መሠረት ክርስቲያኑ እና ሙስሊሙ ወገናችን መከራ እና ደስታን አብሮ የማካፈል፣ እርስ በእርስ የመጠባበቅ እና የመደጋገፍ ረጅም የጋራ ታሪክ ያለው መኾኑን የሚመሰክር ነው። በተጨማሪም የሃይማኖቶቻችን ሁሉ መሠረት ፍቅር፣ ቅንነት፣ በበጎ ነገር መተባበር እና የሰውን ልጅ ክብር ማስጠበቅ መኾኑን ያሳያል፡፡
ይህንን ታላቅ በዓል ስናከብር የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ)
ታላቅ የሥነ ምግባር አርዓያነት እና የሰላም አስተምህሮ መሠረት በማድረግ ጉባኤያችን የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፦
በድጋሚ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ እና ለመላው የክልላችን ነዋሪዎች በሙሉ እንኳን ለ1ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት እና የምህረት ያድርግልን!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ተቋማት ጉባኤ
ባሕር ዳር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
