
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ በመላው ክልሉ አካባቢዎች መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች
በባሕር ዳር ከተማ መስከረም 16 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የምዝገባ መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል።
በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ካገኘናቸው ወላጆች መካከል ወይዘሮ እንያት ተሻገር የሕይወት ውጣ ውረድ እና የኢኮኖሚ ጫና ሳይበግራቸው ማለዳ ተነስተው ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ መገኘታቸውን ተናግረዋል። ወይዘሮ እንያት ለልጆቻቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጹት የነገ ተስፋቸውን ወደሚያለመልሙ ትምህርት ቤቶች በመውሰድ እንደኾነ ገልጸዋል።
“በኢኮኖሚ እና በሌሎች የሕይወት ችግሮች ውስጥ ብንኾንም የልጆቻችንን ትምህርት ማስተጓጎል የነገ ሕይወታቸውን ማጨለም ነው፤ ይህንን በመገንዘብ ቀኑ ሳይረፍድ እና ሳያልፍ ልጆቼን ማስመዝገብ ችያለሁ” ብለዋል።
ሌላኛው የተማሪ ወላጅ አቶ አምላክ ወርቁ የልጆች ትምህርት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሕይወት መዋዕለ ነዋይ እንደኾነ ነግረውናል፡
“ከምንም በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለልጆቻችን ትምህርት ነው፤ ልጅ ተማረ ማለት ቤተሰብ ተለወጠ፣ ሀገርም ተስፋ አገኘች ማለት ነው፤ ስለዚህ ማንኛውም ወላጅ ያሉበትን ችግሮች ተቋቁሞ ልጁን ማስመዝገብ አለበት” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ የትምህርት ዘመኑ ምዝገባ ዛሬ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለመቀበል እና የመማር ማስተማር ሂደቱን ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ወላጆች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ጨምሮ ባሉት የምዝገባ ቀናት እንዲያስመዘግቡም ጥሪ አቅርበዋል።
ሕጻናትን አልባሌ ቦታ ከማዋል ይልቅ በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ ማድረግ የቤተሰብ ብቻ ሳይኾን የጠቅላላው ማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው መሪዎች ኀላፊነት በመኾኑ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
