የኢትዮጵያ ከተሞችን መልክ የገለጠው የኮሪደር ልማት

11
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተተገበሩት እንደ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለትውልድ እና የኮሪደር ልማት ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በማፋጠን እና የከተሞችን ገጽታ በመለወጥ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ በአሁኑ ወቅት በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች በተሳካ ሁኔታ በመተግበር ላይ ይገኛል። የሥራ ጥራት እና ፍጥነትን አጣምሮ የያዘው የኮሪደር ልማት አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ዕድሎችን በመክፈት እና ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር የነዋሪዎችን የኑሮ ዘይቤ በበጎ መልኩ እየቀየረው ይገኛል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተሠራ አንድ ጥናት የኮሪደር ሥራ የትራንስፖርት እና የከተማ መሠረተ-ልማት አውታሮችን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽላል ብሏል። የተሠሩት ማሻሻያዎች ለግል ባለሀብቶች እና ለአነስተኛ ነጋዴዎች አዳዲስ እና የተለያዩ የንግድ አማራጮችን አስገኝተዋል። የኮሪደር መንገዶቹ መዘርጋት ምርት እና አገልግሎት በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ በከተማዋ የተሻለ እና ፈጣን የገበያ ትስስር ፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኮሪደር ልማት ሥራን የሚገልጹት የብዝኀ-ዓላማ ፕሮጀክት በማለት ነው። ይህ ዘመናዊ የልማት ስልት በግንባታ ወቅትም ኾነ ከግንባታ በኋላ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መኾኑ አንደኛው ምክንያት ነው።
ወጣቶች በዩኒቨርሲቲ ከቀሰሙት የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባሻገር በተግባር የተደገፈ የዲዛይን እና የግንባታ ክህሎት እንዲያዳብሩ ትልቅ ዕድል መስጠቱንም አንስተዋል።
በልማቱ አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ በጥቂት ወራት ውስጥ ለፕላስቲክ ቤቶች ምትክ የሚኾኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያዎች መገንባታቸው ለገጽታ ለውጥ ያለውን አበርክቶ ገልጸዋል።
የመንገዱ፣ የመብራቱ እና የአካባቢው መሻሻል የንብረት ዋጋን በእጅጉ ከፍ ስላደረገው ባለሀብቶች በልበ ሙሉነት መዋዕለ ንዋያቸውን ከፍተኛ ገቢ በሚያመነጩ ዘርፎች ላይ እንዲያፈሱ አድርጓቸዋል።
አማራጭ መንገዶችን በመሥራት፣ የእግረኛ እና የመኪና መንገድን በመለየት የትራፊክ መጨናነቅ ችግርን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማቃለሉንም ጠቁመዋል። ይህም ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን እና የእግር ጉዞን የሚያበረታታን አካባቢ ፈጥሯል።
ቀደም ሲል የጤና ስጋት የነበሩ ወንዞች እና የውኃ ዳርቻዎች ዛሬ ለውበት ብቻ ሳይኾን ለከተማው ነዋሪ የሙቀት ማብረጃ፣ የመንፈስ ማደሻ እና መዝናኛ ኾነዋል። ይህ የአረንጓዴ ልማት ስኬት ከተሞችን ከድምጽ፣ ከአየር፣ ከወንዞች እና ከመንገድ ቆሻሻ ብክለት የጸዱ እና ንጹህ እንዲኾኑም አድርጓቸዋል።
ኮሪደር የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን ፍስሰት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ከዚህ ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ አሁን ላይ መጠሪያ ስም ብቻ ሳትኾን በተግባር ያበበች እና የብልጽግና ትልቅ ማሳያ ምልክት መኾኗን ጠቁመዋል። ከተማዋ ለውጭ እንግዶች የመገረሚያ መግቢያ በር በመኾን እንደ አርባምንጭ፣ ሐዋሳ እና ባሕር ዳር ያሉ ሌሎች የሀገሪቱን የልማት መዳረሻዎች እንዲጎበኙ ትገፋፋለች ነው ያሉት።
ማኅበራዊ ግቡን ለማሳካትም መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተለይም ፓርኮችን እና የአነስተኛ እግር ኳስ ሜዳዎችን ግንባታ በአብነት አንስተዋል። ይህም የሕዝቡን ማኅበራዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርግ ኾኖ ይነሳል።
ኮሪደር ወጥ የኾነ የቀለም ወጥነትን፣ የግንባታ ጥራትን እና የብርሃን አቅርቦትን በመጠቀም ከተሞች ንጹህ፣ ስልታዊ እና ውብ እንዲኾኑም እያደረገ ነው። ሌሊት የሚያበሩ መብራቶች መኖራቸው ሰዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እና የደኅንነት ስጋት እንዳይኖርም ከፍ ያለ ፋይዳ እያበረከተ ነው።
የኮሪደር ልማቱ ሕዝቡን አፈናቅሎ አዲስ ከተማ ከመመሥረት ይልቅ ሕዝቡ ባለበት ነባር ከተማን ማዘመን እንደሚቻል ያሳየ ድንቅ ሞዴል መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ኮሪደር የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ኅብረተሰቡ እና ወጣቶች አካባቢያቸውን በባለቤትነት ስሜት የመጠበቅ እና የመንከባከብ በጎ ባሕል እንዲያዳብሩ በር ከፍቷል።
የኮሪደር ልማት በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ ከተሞች በትኩረት እየተሠራበት ሲኾን በአማራ ክልል በ43 ከተሞች በመተግበር ላይም ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
Previous articleግንድ እና ወርቅ ይዞ ከመዞር የታቀበው ወንዝ ዛሬስ?
Next articleልጆቻችሁን ወደ ትምህርት ቤት ላኳቸው።