“ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክር ከኃይል አዙሪት ወደ ሐሳብ ልዕልና ተሸጋግራለች” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

19
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ የዘመናት የፖለቲካ ቁርሾዎቿን እና አውዳሚ የደም አዙሪትን በመስበር በሀገራዊ ምክክር ሂደት አዲስ የዴሞክራሲ እና የሰላም ምዕራፍ መክፈቷን አስታውቋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በሀገራዊ ምክክሩ ከተከናወነው የዝግጅት ምዕራፍ በኋላ 4 ሺህ ወኪሎችን በማሳተፍ ሲካሄድ የቆየው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መጠናቀቁን ገልጿል። ጉባኤው የሀገረ-መንግሥት ታሪካዊ ተቃርኖዎችን በኃይል የመፍታት አውዳሚ ልምድን በማስቀረት፣ በምክክር የፀናች ኅብረ-ብሔራዊት ሀገርን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ መሠረት ጥሏል ነው ያለው አገልግሎቱ።
ምክክሩ ነባሩን የ’አሸናፊ-ተሸናፊ’ የፖለቲካ አካሄድ በመቀየር፣ የሁሉም ወገኖች ድምጽ የተሰማበት እና የጋራ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት አዲስ የሰላም ውል እውን መሆኑን አመላክቷል። ሂደቱ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ጥበብ የመፍታት አቅማቸውን ለዓለም ያሳዩበት እና በአህጉራዊ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ሰነድ እንዲዘጋጅ ስለማስቻሉም ተብራርቷል።
ከዚህ በኋላ የትኛውም አካል ለግጭት እና ለአመጽ ማስተንፈሻ ‘የውይይት መድረክ አጣሁ’ የሚል ምክንያት ሊኖረው እንደማይችል በተግባር ተረጋግጧል ነው ያለው።
መንግሥት ለሂደቱ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን እና በቀጣይም በምክክር የተከፈተው በር ዘላቂ የሰላም ማዕቀፍ ኾኖ እንዲቀጥል፣ የፖለቲካ አውዱ ከነፍጥ ኃይል ወጥቶ በይቅርታ እና በሀሳብ ልዕልና እንዲመራ አስፈላጊው ሁሉ እንደሚደረግም ነው ያስታወቀው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከ562 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘው ጸጋ ምንድን ነው?
Next articleሚስ ሻደይ የቁንጅና ውድድር እየተካሄደ ነው።