
ምክትል ጠቅላይ ተመስገን ጥሩነህ 13ኛውን የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ 13ኛውን የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከፍተናል ብለዋል።
አፍሪካውያን በራስ አቅም የጤና ሉዓላዊነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል ነው ያሉት። ከ130 ዓመታት በፊት ቀደምት ኢትዮጵያውያን በዓድዋ በአይበገሬነት ያስመዘገቡት ድል፣ ዛሬ የሕዝባችንን ጤና በራስ አቅም የመጠበቅ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ መደገም አለበት ብለዋል።
የጤና ሉዓላዊነት ማለት መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን በራሳችን የማምረት፣ የጤና ባለሙያዎቻችንን የማሠልጠን፣ የማቆየት፣ ወረርሽኞችን ወይም የጤና ቀውሶችን የዓለምን እጅ ሳንጠብቅ በራሳችን የመቋቋም ብቃት መፍጠር ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን አፍሪካዊ ዓላማ ለማሳካት የመድኃኒት፣ የመመርመሪያ ቁሳቁሶች እና የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረትን እያጠናከረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
አዲስ አበባን አፍሪካውያን ጥራት ያለው እና የላቀ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙባት የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ሆስፒታሎችንና የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ናት ብለዋል።
መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ አቅሞችን በመጠቀም የማይበገር የጤና ሥርዓት መገንባቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በጤናው ዘርፍ የግል ባለሀብቶች ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው የሚሠሩበት አህጉራዊ መድረክ እንዲኖር፣ የአፍሪካ ጤና ጥበቃ ፌዴሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲመሠረት መንግሥታችን ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
