በበየዳ ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።

5
በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ ወረዳ በተከዜ፣ በበስቂያ፣ በጠዘን፣ በሰገነት እና በሌሎች ጫካዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።
የሰላም ጥሪውን ከተቀበሉት መካከል በታጣቂዎች አደረጃጀት የብርጌድ አዛዥን ጨምሮ ሌሎች ታጣቂዎች ይገኙበታል። ታጣቂዎቹ የቡድን እና የነፍሰ ወከፍ ትጥቆችን ይዘው ነው የሰላም አማራጭን የተቀበሉት።
የበየዳ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሸጋው ብርሃን እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ተስፋሁን ቤኬ የሰላም አማራጭን ለተቀበሉት ታጣቂዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሥራ ኀላፊዎቹ የእርስ በእርስ ግጭቱ ከኪሳራ ውጭ ምንም ጥቅም እንደሌለው እና የአካባቢውን ዕድገት ወደኋላ እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የተመለሱትን አመስግነዋል። አሁንም በጫካ የሚገኙ ሌሎች የታጠቁ አካላት ተመሳሳይ የሰላም አማራጭ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉት ታጣቂዎች ቀደም ሲል ወደ ጫካ መውጣታቸው የተሳሳተ መንገድ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ ሰላምን መምረጣቸው ትክክለኛ ውሳኔ መኾኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ በልማት እና በሰላም ግንባታ ላይ በንቃት በመሳተፍ የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዕድል እና ስጋት፦
Next article“አፍሪካውያን በራስ አቅም የጤና ሉዓላዊነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ