
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቴክኖሎጂ እድገት በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል።
በትምህርት፣ በሕክምና፣ በንግድ፣ በዲጂታል ባንክ፣ በግብርና እንዲኹም በመረጃ ተዳራሽነት ረገድ የሰዎችን እንግልት በመቀነስ እና ጊዜን በመቆጠብ በኩል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ ውስብስብ የሥራ ሂደቶችን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ነገር ግን ቴክኖሎጂው በክፉ እጆች ውስጥ ሲወድቅ ማኅበረሰቡን ለከባድ አደጋ እና ሥጋት መዳረጉ አይቀሬ ነው።
ለዚህም ማረጋገጫ የሚኾነው ቢቢሲ ያወጣው የኤልዛቤጥ ቤንዝ ገጠመኝ አንዱ ማሳያ ነው።
እ.አ.አ መስከረም 2025 ኤልዛቤጥ ቤንዝ የ16 ዓመት ልጇ ጆን በስልክ መስመር “እናቴ፣ ጓደኛዬ ሞተ!” እያለ ሲያለቅስ ሰማች። እናት በድንጋጤ ተዋጠች፤ ነገር ግን ነገሩ በዚህ አላበቃም።
አንድ እንግዳ ሰው በልጁ ስልክ የልጇን ጓደኛ እንደገደለውና በሚቀጥሉት 20 ደቂቃዎች ውስጥ 7 ሺህ 500 ዶላር ካላመጣች በልጇ ላይም ተመሳሳይ አደጋ እንደሚያደርስበት አስፈራራት።
እናት በድንጋጤ ገንዘቡን ልታስረክብ ስትጣደፍ የልጇ ታላቅ ወንድም ደውሎ ልጁ እግር ኳስ ጨዋታ ላይ በሰላም እንደሚገኝ ነገራት።
በስልክ የተሰማው የለቅሶ ድምጽ ሲረጋገጥ ሙሉ በሙሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተቀናጀ የሐሰት ድምጽ (Deepfake) ነበር።
ስለዚህ ማኅበረሰቡ እራሱን እንዲጠብቅ የሚከተሉትን ዋና ዋና የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወስድ ይመከራል።
#የአጭበርባሪዎችን ዋና ዋና ምልክቶች መለየት፦
ክሪፕቶ ከረንሲ (Bitcoin)፣ የቨርቹዋል ስጦታ ካርዶችን (Gift Cards) እና መሰል መንገዶችን በመጠቀም ክፍያ እንዲላክላቸው ይጠይቃሉ።
ከቤተሰብ አባላት ጋር አስቀድሞ ድገተኛ አደጋ ሲያጋጥም ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያገለግል ምስጢራዊ ቃል ማዘጋጀት ይመከራል። ቃሉ ለቤተሰቡ ለማስታወስ ቀላል፣ ለባዕድ ሰው ግን በፍጹም የማይገመት መኾን አለበት።
የቤተሰብ አባል ይኹን አይኹን ለማረጋገጥ አስቀድሞ የተዘጋጀውን ምስጢራዊ ቃል መጠየቅ ይገባል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
