
13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው አዲስ አበባን በልዩ የጤና አገልግሎት እና በሕክምና ቱሪዝም ዘርፍ ቀዳሚ የአፍሪካ መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሠራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
በየዓመቱ በርካታ አፍሪካውያን ሕክምና ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገራት በመጓዝ ሀብት እንደሚያባክኑ የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአህጉሪቱን የጤና አቅም መቀየር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት እና የአፍሪካ ሲዲሲ መቀመጫ መኾኗ የአፍሪካውያን ኩራት የኾነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያላት እና የእንግዳ መስተንግዶ መሠረተ ልማቷ ለዚህ ዓላማ ጠንካራ መሠረት እንደሚኾኑ ጠቁመዋል።
የሕክምና ቱሪዝም እንዲያድግ ከመጓጓዣ በላይ የሕክምና ጥራት፣ የታካሚ ደኅንነት እና የሕዝብ እምነት ወሳኝ መኾናቸውን አመላክተዋል።
በሌላ በኩል አፍሪካ በጤና ምርቶች ላይ ከውጭ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ መድኃኒት፣ የምርመራ መሳሪያ ምርቶች እና የሕክምና መሣሪያዎችን በአህጉሪቱ ውስጥ ማምረት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም የሀገራት የጤና መስፈርቶችን ማጣጣም፣ የጋራ ግዥን ማስፋት እና የክልላዊ ገበያን ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑን አስታውቀዋል።
መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በጤና ዘርፍ ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። መንግሥት የሕዝብ ጤናን የመጠበቅ ኀላፊነቱን ሲወጣ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ በማምጣት የጤና ሥርዓቱን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የዓድዋ የአንድነት እና የራስን ዕጣ ፈንታ የመወሰን መንፈስን በመጥቀስ አፍሪካ የጤና ቀውሶችን ብቻ የምትቋቋም ሳይኾን የጤና ፈጠራን የምትመራ፣ የራሷን የጤና ምርቶች የምታመርት እና የሕዝቦቿን ጤና በራሷ አቅም የምታስጠብቅ አህጉር እንድትኾን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ: ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
