
የአፍሪካ የጤና ችግሮች የሀገር ድንበር የማያውቁ በመኾናቸው የአህጉሪቱ ሀገራት በጋራ መሥራት እና የጤና ሥርዓታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት በ13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ኤግዚቢሽን ላይ ነው። “የምሥራቅ አፍሪካን የጤና ኢኮኖሚ መገንባት” የሚለው የጉባኤው መሪ መልዕክት ወቅታዊ እና ትልቅ ዓላማ ያለው መኾኑንም ጠቁመዋል።
የጤና ደኅንነት፣ የጤና ፋይናንስ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓት አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ የጋራ ትብብር የሚፈልጉ ጉዳዮች መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የጤና አገልግሎትን በማስፋፋት፣ የጤና መሠረተ ልማት እና የሰው ኀይልን በማሳደግ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን በማጠናከር ዕድገት ማስመዝገቧን ገልጸዋል። በተለይም የእናቶች እና የሕጻናት ጤና ላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።
ነገር ግን የተገኙ ውጤቶች በቂ እንዳልኾኑ ገልጸዋል። ቀጣዩ ትኩረት የጤና አገልግሎቱን ጥራት፣ ተደራሽነት እና ውጤታማነት ማሻሻል መኾኑን አመላክተዋል።
ዲጂታል ጤና እና ቴሌ-ጤና እየተሥፋፉ በመኾናቸው የጤና ሥርዓቱ ከቴክኖሎጂ ለውጥ ጋር መራመድ መጀመሩንም ተናግረዋል። በተጨማሪም የ“አንድ ጤና” አቀራረብን በማጠናከር የሰው፣ የእንስሳት እና የአካባቢ ጤናን በተቀናጀ መልኩ ማየት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይ ቀጣናዊ የመድኃኒት እና የሕክምና ምርት ማምረት አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል። የኮረና ወረርሽኝ በውጭ የመድኃኒት አቅርቦት ላይ መመርኮዝ የሚያመጣውን ተጋላጭነት እንዳሳየ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በመድኃኒት፣ በሕክምና መሣሪያ እና በምርምር ዘርፍ የሀገር ውስጥ አቅሟን እያሳደገች መኾኗን አስረድተዋል።
መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በጤና ዘርፉ ላይ በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በግሉ ዘርፍ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን በማምጣት የጤና ሥርዓቱን ማጠናከር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ለአፍሪካ የጤና ችግሮች መፍትሔው በጋራ መሥራት እንደኾነም አብራርተዋል።
ዘጋቢ: -ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
