
ድካማቸው እና ጥረታቸው በየመንገዱ በሚዘረጉ ሕገ ወጥ ኬላዎች ከንቱ የኾነባቸው አልሚ ባለሀብቶች እና ነጋዴዎች ሲማረሩ ይሰማል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በግብርና ልማት ላይ የተሰማሩት አቶ ማስተዋል ማዘንጊያ በብዙ ወጭ እና ድካም ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ በሚያደርጉት ጉዞ የሚያጋጥማቸው ፈተና የብዙዎችን እጣ ፈንታ የሚያንጸባርቅ ነው።
እንደ አቶ ማስተዋል ገለጻ በገንዳ ውኃ እና አብርሐጅራ ከተሞች የተዘረጉ ሕገ ወጥ ኬላዎች ዛሬም ድረስ አልተነሱም። የቁም እንስሳት፣ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በሚጭኑበት እና በሚያራግፉበት ወቅት ምንም ዓይነት የታሪፍ ምጣኔን መሠረት ያላደረገ ያልተገባ ክፍያ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።
“በብዙ ወጭ እና ድካም ያመረትነውን ምርት በወቅቱ ወደ ገበያ አውጥተን በተሻለ ዋጋ እንዳንሸጥ ተደርገናል” ነው ያሉት።
በመኾኑም መንግሥት እነዚህን መሰናክሎች በአስቸኳይ በማስወገድ የአልሚዎችን እና የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ይጠይቃሉ።
ለችግሩ ዕውቅና የሰጡት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ የገቢ ተቋማት ገቢ ለመሠብሠብ በሚል በየመጫኛ እና ማውረጃው ሕገ ወጥ ክፍያ ሲያስከፍሉ መቆየታቸውን ያረጋግጣሉ።
ይህ ድርጊት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት እንቅስቃሴን በማስተጓጎል፣ የምርት ዋጋ እንዲጨምር እና የኑሮ ውድነት በሕዝቡ ላይ እንዲባባስ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩንም ጠቁመዋል።
ችግሩን ሥር ነቀል በኾነ መንገድ ለመፍታት የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኀይል ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ፈንታው እስከ አሁን ባለው እርምጃ 164 ሕገ ወጥ ኬላዎችን ማስነሳት መቻሉን እና በአሁኑ ወቅት የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ኾኖም ግን አሁንም በምዕራብ ጎንደር እና በሌሎችም አንዳንድ አካባቢዎች “ለሥራ ዕድል ፈጠራ” እና ለሌሎች ምክንያቶች በሚል ሕገ ወጥ ኬላዎችን የመዘርጋት ሁኔታዎች እንደቀጠሉ የሚያሳይ ጥቆማ እየደረሳቸው መኾኑን አክለዋል።
“ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ውጭ በክልሉ የሚገኝ የትኛውም የገቢ ተቋም ኬላ ዘርግቶ ገቢ የመሠብሠብ መብትም ኾነ ሕጋዊ ተልዕኮ የለውም፤ ከጉምሩክ ውጭ ኬላ መዘርጋት ሙሉ በሙሉ ወንጀል ነው!” ብለዋል።
መንግሥት በእነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል በመግለጽ ኅብረተሰቡም ከጉምሩክ ውጭ የሚዘረጉ ሕገ ወጥ ኬላዎችን በጋራ ሊያወግዝ እና ሊታገል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
