እየጨመረ የመጣው የክልሉ ሕዝቡ ድጋፍ

10
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ ኀይሉ የሕግ ማስከበር ሥራ እና ሕዝባዊ ድጋፉን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከዚህ ቀደም በክልሉ የነበረው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ሕዝቡን ለከፍተኛ ብሶት እና ምሬት ዳርጎት እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ እንዳገለላቸው ተናግረዋል።
ጽንፈኛ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የመንግሥት የጸጥታ ኀይል ሁለንተናዊ ብቃት እንዲጎለብት መደረጉን አንስተዋል። የሰላም አስከባሪውም በትጥቅ እና በቁጥር አቅሙ እንዲጠናከር ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት የጠላትን ቅስም የሚሰብሩ ጠንካራ ሕግ የማስከበር እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ታጣቂ ቡድኑ ተስፋ የቆረጠ፣ ቆሞ መዋጋት እና የጸጥታ ኀይሉን ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ሕዝቡ ከመንግሥት የጸጥታ ኀይል ጎን በመቆሙ እና ጽንፈኛ ቡድኑን በማግለሉ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ጽንፈኛ ቡድኑ ከተለያዩ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ የመሠረተውም አቅም በማጣቱ ነው ብለዋል። በአማራ ሕዝብ ላይ ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት እየሠራ ነው ያሉት ክሚሽነሩ እዚህ ግባ የሚባል ችግር መፍጠር እንደማይችልም ተናግረዋል።
የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን እየተጋ የሚገኘው የሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ ኀይልን በተለያዬ መልኩ መደገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሕዝቡ ለሚሊሻው እና ሰላም አስከባሪው የሚያደርገው ድጋፍ ጠንካራ ነው ብለዋል።
በኹሉም አቅጣጫ የሚገኘው የአማራ ክልል ሕዝብ ሀብት እና ንብረታቸውን በመጠበቅ፣ መሬታቸውን በማረስ እና በመዝራት፤ አዝመራቸውን በመሠብሠብ፤ ቁሳቁሶችን ጭምር በማቅረብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ ክረምትም ሕዝቡ በተደራጀ መንገድ የሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪዎችን ማሣ መዝራት ችሏልም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሕዝብ ለሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪው አልባሳትን በመግዛት፣ ሬሽን በማቅረብ፤ በገንዘብ እና በጉልበት ለመደገፍ የሰሰተው ነገር የለም ብለዋል። ባሳለፍነው በጀት ዓመት ብቻ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ለሚሊሻው እና ሰላም አስከባሪው ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት። ይህ ለሥልጠና፣ ለምግብ፣ ለወታደራዊ አልባሳት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የዋለ ነው ብለዋል።
ሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ የሕዝቡ የሰላም ዋስትና በመኾኑ የነበረው ጠንካራ ሕዝባዊ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት። እንደ ማንኛውም አርሶ አደር መሬቱን በወቅቱ መዝራት፣ ማረም፣ ማጨድ እና መሠብሠብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ ልጆች በወቅቱ ተመዝግበው፣ የትምህርት ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው እንዲማሩ በኹሉም አቅጣጫ ሕዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።ሕዝቡ የጽንፈኛ ኀይሎችን እንቅስቃሴ ለጸጥታ ኀይሉ መረጃ የመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ሕዝቡ ለጸጥታ ኀይሉ የመረጃ ምንጭ መኾን እና የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እንዲመለሱ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጽንፈኝነትን ማከም የሚቻለው ሕዝባዊ መሠረት እንዳይኖረው በማድረግ ነው።
Next articleዜጎች ችግሮችን በጋራ ሲፈቱ የአንድነት መንፈስ ይጠናከራል።