
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎች ዙሪያ ከከተማ፣ ከክፍለ ከተማ እና ከቀበሌ መሪዎች ጋር ተመካክሯል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በችግሮች እየተፈተነች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከእነዚህ ፈተናዎች መውጫ መንገዶችን ፍለጋ እየመከረች መኾኗን አስገንዝበዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ መሪዎች የችግሮቹን ምንጭ እና አቅጣጫ በተለይም ጽንፈኝነት ከየት ወዴት እየሄደ እና ምን ዓይነት ቀውሶችን እየፈጠረ መኾኑን መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ጽንፈኛ ኀይል እና ሥብሥብ ሀገርን ለማፍረስ ከንቱ ምኞት ያዘለ ጥምረት ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተለይም ሕወሃት የሚመራው ይህ የጥፋት ጥምረት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች “የሕዝብ ወኪል እና ነጻ አውጭ ነኝ” በሚል ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችን በማስተባበር አጀንዳውን በቀጥታ ሀገርን ወደ ማፍረስ የቀየረበት ሁኔታ በግልጽ እየታየ ነው። ይህን አደገኛ አካሄድ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በውል ተገንዝቦ የጋራ ትግል ሊያደርግበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጽንፈኝነትን ማከም የሚቻለው ሕዝባዊ መሠረት እንዳይኖረው በማድረግ ነው ብለዋል። ይህ የጥፋት ኃይል እያደረሰ ያለው ጉዳት ተጨማሪ ዕድሜ እንዳያገኝ እና ለሀገር ጠንቅ እንዳይኾን ቀድሞ በማረም መላው ሕዝብ በአንድ ድምጽ ሊታገለው ይገባል ብለዋል።
ትላልቅ የዓለም ፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር እና የፀጥታ ስጋት ለመፍጠር እነዚህን የጥፋት ኀይሎች እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙባቸው ነውም ብለዋል። በአሁኑ ዘመን የውጭ ወረራ ሲባል እነዚህን የውስጥ ጽንፈኞች እንደ ፈረስ እየጋለቡ እና ዓለም አቀፍ ጫና በመፍጠር ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ የተቀናጀ እንቅስቃሴ መኾኑን መረዳትም ያስፈልጋል።
ውሥብሥቡን የውስጥ እና የውጭ ሴራ በማክሸፍ ረገድ ትልቁ ኀላፊነት የሚወድቀው በመሪዎች እና በሕዝቡ ላይ ነው ብለዋል። መሪዎች የተረዱትን እና ያወቁትን እውነት መሠረት በማድረግ መላው ሕዝብ ለሀገር አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላም እና ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስኬት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ በቂ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውስጥ እና ከውጭ ስጋቶች ታድጎ ሰላምን ማረጋገጥ ዋነኛ የሕዝብ አደራቸው መኾኑን ገልጸዋል።
መላው ማኅበረሰብም ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጠንካራ አንድነቱን ጠብቆ ክልሉን ከጥፋት እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
