የ “ነጭ ወርቅ” ሰብሎች ከ780 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝተዋል።

5
የኢትዮጵያ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ላኪዎች ማኅበር በአኩሪ አተር እና በሰሊጥ ምርቶች በተሻሻለ የግብርና ምርታማነት ዙሪያ የጥናት ወርክሾፕ አካሂዷል።
በወርክሾፑ የሰሊጥ እና የአኩሪ አተር ምርታማነትን ለማሳደግ እና በተሻሻለ መንገድ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ የሚያግዙ ጥናቶች ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ላኪዎች ማኅበር የቦርድ አባል ሀይደር ከማል በ2018 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች 780 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል።
ከዚህ ውስጥ አኩሪ አተር እና ሰሊጥ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ነው ያሉት። በቀጣይም ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለውጭ ገበያ ያላቸውን ድርሻ ለመጨመር የተጠኑ ጥናቶችን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የተገኙ ጥናቶችን ለእርሻ ምርታማነት፣ ለምግብ ተደራሽነት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ ለመተግበር በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት ሙሽራ ሲሳይ እንደገለጹት በአማራ ክልል “የነጭ ወርቅ ምድር” በሚባሉ አካባቢዎች የሰሊጥ ምርት በስፋት ይመረታል።
ክልሉ ከፍተኛ የሰሊጥ እና የአኩሪ አተር ምርቶችን እያመረተ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የዘርፉን ምርታማነት ለማሻሻል የሚደረጉ ችግር ፈቺ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ላኪዎች ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ስሜነህ ቤሴ(ዶ.ር) ወርክ ሾፑ አርሶ አደሮችን የተሻሻለ የግብርና አመራረትን እንዲተገብሩ እና በገበያ ሥርዓቱ የእሴት ሰንሰለት እንዲጨምሩ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል መዘጋጀቱም ክልሉ በአብዛኛው የሰሊጥ እና የአኩሪ አተር ምርት ምንጭ በመኾኑ ነው ብለዋል። ጥናቱ ለመንግሥት የፖሊሲ ግብዓት እንደሚኾንም ይጠበቃል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበኢትዮጵያ የሙዝ ምርት የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል።
Next articleጽንፈኝነትን ማከም የሚቻለው ሕዝባዊ መሠረት እንዳይኖረው በማድረግ ነው።