በኢትዮጵያ የሙዝ ምርት የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል።

17

 

የኢትዮጵያ አበባ አትክልት እና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) አምራች ላኪዎች ማኅበር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የሙዝ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ሙዝ ምርት እና ጥራት ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጉባኤው የሙዝ እሴት ሰንሰለት፣ ድኅረ-ምርት አያያዝ እና የዓለምአቀፍ ገበያ ላይ ትኩረት አድርጓል።

የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ዘውዴ በኢትዮጵያ የሙዝ ምርት ሂደት የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በየጊዜው በሙዝ እሴት ሰንሰለት፥ በቅድመ ሥራ፣ በድኅረ ምርት አያያዝ እና በዓለምአቀፍ ገበያዎች ላይ ተወዳዳሪ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ይህ መድረክ መዘጋጀቱም የተጀመሩ በጎ ሥራዎችን ለማጠናከር እና የበለጠ ውጤታማነታቸውን ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ሶፊያ ካሣ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ አትክልት እና ፍራፍሬ በማምረት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በሙዝ ምርት እና ንግድ የተሻለ ዓለምአቀፍ ንግድ ግብይት ያላት ሀገር መኾኗን ያነሱት ሚኒስትር ድኤታዋ ሙዝን ከአመራረት እስከ ምርት አስተሻሸግ ድረስ ለጥራት ትኩረት በመስጠት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አምራቾች የሙዝ ምርትን በጥራት በማምረት ለገበያ እንዲያቀርቡ ከአመራረት እስከ ምርት አስተሻሸግ ድረስ በቂ ሥልጠና መሰጠት እና ገበያን የማመቻቸት ሥራዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይሠራል ነው ያሉት።

ሙዝ አምራቹ እንደሀገር በጥራት ጉድለት ምክንያት የሚያጣውን ጥቅምም እንዲያገኝ የሚያስችል ሥራን በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

#አሚኮ #የሙዝምርት_ጥራት #ኢትዮጵያ🇪🇹

#አዲስ_አበባ #ነሐሴ_14_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleያልተረጋገጠ መረጃ ጥፋት
Next articleየ “ነጭ ወርቅ” ሰብሎች ከ780 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝተዋል።