
የ”መደመር” እሳቤ የትብብር፣ የመተማመን፣ የአንድነት እና የጋራ ኀላፊነት መርህን በማጠናከር የሀገር ግንባታን ለማፋጠን የሚያበረታታ ነው።
መደመር ልዩነትን ወደ ጋራ ጥቅም የሚቀይር እሳቤ እንደኾነው ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ይህንን ፍልስፍና በተግባር ያንጸባርቃል።
ዜጎች ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን በማዋሃድ የማኅበረሰብን ችግሮች በጋራ ሲፈቱ የአንድነት መንፈስ ይጠናከራል፣ የመተማመን ባሕልም ይጎለብታል።
በመደመር መንግሥት ዘመን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከግለሰብ ተሳትፎ ባለፈ የሀገራዊ እንቅስቃሴ መልክ ይዞ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህ ረገድም መርሐግብሩ በሐረሪ ክልል የመደመርን ፍልስፍና በተግባር በሚያንፀባርቅ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
በዚህም በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሰው ተኮር ሥራዎች እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግበዋል።
ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሐ ግብሮች በክልሉ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ እና የመገንባት ሥራዎችን፣ የትምህርት ቤቶችን እና የጤና ተቋማትን የማደስ ሥራዎች ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ከመተከላቸውም ባሻገር የነፃ ሕክምና አገልግሎት፣ የአካባቢ ጽዳት እና የቆሻሻ ማስወገድ ሥራዎች በበጎ ፍቃደኞች ተከናውነዋል።
ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች ማዕድ ማጋራት፣ የአልባሳት እና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ፣ የደም ልገሳ ተግባርም በሰፊው ሲከናወን ቆይቷል።
ለተማሪዎች እና ለትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የትምህርት ቤት ግንባታ እና እድሳት፣ የቤተ መጻሕፍት ማደራጀት የመሳሰሉ ተግባራት በበጎ ፈቃደኞች ተከናውነዋል።
ይህ የበጎ ፍቃድ ባሕል በዘንድሮው የክረምት ወራት በ14 የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህም ለዘላቂ ልማት፣ ለማኅበራዊ አንድነት እና ለሀገራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የክልሉ መንግሥት በመደመር መንግሥት ሰው ተኮር እሳቤዎች የጀመራቸውን ስኬታማ ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
