
የአሱሪቲ በዓል ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ገልጿል።
የዘንድሮው የአሱሪቲ በዓል ከነሐሴ 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጳጉሜን መጨረሻ ድረስ በልጃገረዶች እና በታዳጊ ወጣቶች ጥበባዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ይከበራል ተብሏል።
አሱሪቲ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ልጆች በሀገርኛ አልባሳት ደምቀው በባሕላዊ ጭፈራ ታጅበው በየቤቱ እየዞሩ አዲስ ዓመት መድረሱን የሚያበስሩበት የመልካም ምኞት መግለጫ በዓል ነው።
በዚህ በዓል ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 18 ዓመት ያሉ ልጃገረዶች እንግጫ በወገባቸው ያስራሉ፣ ወንዶቹ ደግሞ የእንግጫ ጉንጉን ከእርጥብ ሳር ጋር ጨምረው በመያዝ በየቤቱ እየዞሩ እንኳን አደረሳችሁ እያሉ በቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ። የቤቱ አባውራ ወይም እማውራም በምላሻቸው እሸት መድረሱን የሚያበስሩ እንደ በቆሎ እሸት፣ ቡያ፣ ዱባ ወይም ሌላም ቤት ያፈራውን ስጦታ በማበርከት በደስታ ያከብሩታል።
በዓሉ ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የባሕል ጥናት ከሚሠሩ ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች ልማት ቡድን መሪ ወለሊ ገልጸዋል።
በእንጅባራ ከተማ የሚገኙ ልጃገረዶችም አሱሪቲ እርስ በዕርስ የሚተዋወቁበት የፍቅር እና የአንድነት በዓል በመኾኑ ዕለቱን በጉጉት እንደሚጠብቁት ተናግረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከሃሊ በዓሉ ለአዲስ ዓመት ተስፋ የሚደረግበት እና የጎላ ማኅበራዊ መስተጋብር የሚንፀባረቅበት መኾኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የአሱሪቲ በዓል ከነሐሴ 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጥበባዊ ክዋኔዎች ታጅቦ በድምቀት እንዲከበርም ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
