የሶለል በዓልን በራያ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።

9
🌼ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ደመናው እየገፈፈ ሲሸሽ፣ ፀሐይም ሙሽራ መስላ ትገለጣለች፤ መሬት በአረንጓዴ ተውባ የልምላሜ ልብሷን ትለብሳለች፤ ጋራው እና ሸንተረሩ በአበቦች ማሸብረቅ ይጀምራሉ።
በዚህ ወቅትም ልጃገረዶች ዓመቱን ሙሉ ሲናፍቁት የከረሙትን ባሕላዊ ጨዋታ የሚጫወቱበት የአሸንድዬ ቅጠልም ይለመልማል። 🌸🌿
ይህን አሸንድዬ ቅጠል ልጃገረዶች በሚያምር የባሕል ቀሚሳቸው ላይ በወገባቸው ታጥቀው
“አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ፤
ፈስስ በይ በቀሚሴ” እያሉ የሶለል በዓላቸውን የሚያደምቁበት ነው።
ሶለል በራያ አካባቢ በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ ልጃገረዶች የሚጫወቱት ባሕላዊ ክዋኔ ነው። የራያ ልጃገረዶች ተውበው፣ አምረው እና ደምቀው የሶለል በዓላቸውን የሚያከብሩበት የዓመቱ ልዩ ወቅትም ነው። ይህ ወቅት በዓሉን ለማክበር በጉጉት የሚጠብቁትም ነው።
በዘንድሮው ዓመትም የሶለል በዓል በሁሉም የራያ አካባቢዎች በድምቀት ለማክበር ዝቅጅት መጠናቀቁን የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ ተናግረዋል።
ሶለል ልጃገረዶች በነቂስ ወጥተው በነጻነት በአደባባይ የሚያከብሩት በዓል በመኾኑ ዕሴቱን እና ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት ኀላፊዋ።
በዓሉን በድምቀት ለማክበር በየወረዳዎች የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም፣ ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር፣ በፓናል ውይይት፣ በጎዳና ላይ ትርዒት እና በሌሎችም መርሐ ግብሮች በድምቀት እንደሚከበር አስታውቀዋል።
📍ሶለል ከባሕል መገለጫነት ባለፈ የራያዎቹ ልዩ መልክ፣ ውበት፣ ድምቀት ነውና በዓሉን በራያ ምድር ተገኝታችሁ አድምቁ፡፡
ዘጋቢ፡- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየማይረሳው ቁስል