
ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባለው የትግል እና የሥልጣን ጉዞው ውስጥ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ከግል እና ከቡድናዊ ዓላማው በታች በማድረግ በርካታ የፖለቲካ እና የጂኦፖለቲካ ሴራዎችን ሲፈጽም ቆይቷል።
የተከዜ ፖለቲካ መጽሐፍ ደራሲ ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) ሕገ ወጥ ቡድኑ ከትናንት እስከ ዛሬ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ የውጭ አጀንዳዎችን እና ጫናዎችን በሀገሪቱ ላይ የማስፈጸም ባሕሪውን እያንጸባረቀ መኾኑን ይገልጻሉ። በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ሴራዎችን ሲጎነጉን የቆየ ቡድን እንደኾነም ነው የተናገሩት።
በተከዜ ተፋሰስ ያለውን እምቅ ሐብት ለመቆጣጠር ጥንተ ጠላት ከኾኑ ሀገሮች ጋር በመሥማማት መሬትን ቆርሶ ለመስጠት እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ደፋ ቀና እያለ ያለ ቡድን መኾኑንም አንስተዋል።
ከሥልጣን ከወጣ በኋላ የግል ፍላጎቱን ለማሟላት በወሎ፣ በመተከል፣ በአፋር፣ በሶማሊያ እና በኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰቱ የወሰን እና የማንነት ግጭቶችን በመለኮስ ሰፊ ዎጋ እያስከፈለ መኾኑንም ተናግረዋል።
በተለይም የወልቃይት አካባቢዎችን ያለ ሕዝብ ፍላጎት በካርታ ወሰን ውስጥ በማካተት ከፍተኛ የማንነት ማጥፋት ዘመቻ አካሂዷል ነው ያሉት። የአካባቢው ተወላጆች በቋንቋቸው እንዳይናገሩ ተደርገዋል፤ በማንነታቸው በደል ሲፈጽም የቆኖ ቡድን ነው ብለዋል።
ታላላቅ የታሪክ አዋቂዎች ልቅም ብለው ታድነው ደብዛቸው እንዲጠፉ ተደርጓል ነው ያሉት። ነዋሪዎች ለአካባቢያቸው ባዳ እንዲኾኑ ማድረጉም የቅርብ ትውስታ እንደኾነ ነው የገለጹት።
በተለይም “አማራ ነን” ያሉ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ሱዳን እና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሰደዱ ተገድደዋል፤ በምትኩ ሌላ ማኅበረሰብ እንዲሰፍር በማድረግ ሥነ-ምሕዳራዊ ለውጦችን ለመሥራት ጥረት አድርጓል ነው ያሉት።
በማይካድራ እና በሌሎች የወልቃይት አካባቢዎች የተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር የማይረሳቸው ተግባር ነው ይላሉ።
በአጠቃላይ ሕዝቦች ተፈናቅለዋል፤ ተገድለዋል፤ ተሠድደዋል ደብዛቸው ጠፍቷል፤ ግፍ እና በደልን ፈጽሟል ብለዋል። በመላ ሀገሪቱ የለኮሰው እሳት የግጭት ምንጭ እንዲኾን አድርጓል ነው ያሉት። በዚህ አካባቢ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲርቁ እንዳደረገም አንስተዋል። የሥነ ልቦና ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ታሪክ የማይረሳው ተግባር ነው ብለዋል።
ይሁንና የአካባቢው ሕዝብ በጠንካራ ተጋድሎ እና ሌሎች ንቅናቄዎች ማንነቱን እና መሬቱን ከትናንት እስከ ዛሬ እያስከበረ ይገኛል። አካባቢው የክልል ብቻ ሳይኾን የጠቅላላ ሕዝብ እና የሀገር ህልውና ጉዳይ መኾኑንም አጽንኦት ሠጥተዋል።
ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) እንደገለጹት ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የሴራ ጥንስስ ከጅምሩ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እና ቡድኖች ጋር አብሮ በመሰለፍ የውጭ ተልዕኮዎችን የማሥፈጸም እና የውጭ ድጋፎችን በመጠቀም የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ምህዳር ሲያምስ ኖሯል፤ ይህም የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት የሚዳርገው ተግባር ነው፤ ባሕሪው ዛሬም ድረስ ቀጥሏል ነው ያሉት።
ይህን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥን ተግባር ለማምከን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። ሁሉም ሕዝብ የቡድኑን አጥፊ ተግባራት በጋራ በመቃወም ድርጊቱን ማውገዝ እና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
ሕዝቡም በአጥፊ ቡድኖች ሳይደናገር እውነታውን በመገንዘብ ተቀናጅቶ መታገል ይኖርበታል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
