ሻደይ የሰላም ምልክት

2
የዘንድሮው የሻደይ በዓል “ሻደይን እናከብራለን፤ እሴታችንን እንጠብቃለን” በሚል መሪ መልዕክት ከነሐሴ 16/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል።
በዓሉን የሚያደምቁ የሻደይ ቆነጃጅትም ከተለያዩ ወረዳዎች ወደ ሰቆጣ ከተማ መግባት ጀምረዋል።
የጻግቭጅ ወረዳ የሻደይ ተጫዋች የኾኑት ግብጻት ኽንዲ እና ዘውድ ሰፊው በዓሉ ሰላም የሚሰበክበት እና እህትማማችነት የሚጸናበት መድረክ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰላም ምልክት የኾነውን የሻደይ ቅጠል በወገባቸው በማሰር በዓሉን ለማድመቅ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።
የጻግቭጅ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ተወካይ ብርሃነመስቀል ሚሰነ በወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ሥነ-ልቦና ለመጠገን እና የጻግቭጅን ባሕላዊ እሴት ለማሳየት በዓሉ ትልቅ አጋጣሚ መኾኑን ገልጸዋል።
ከሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ መሥተዳድሮች የተውጣጡ ተጫዋቾች ወደ ሰቆጣ እየገቡ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ይርጋ ማርዬ ናቸው።
የማንነት ጥያቄ ባሉባቸው እንደ ኮረም፣ ዛታ እና ወፍላ ባሉ ወረዳዎች ያሉ ተጫዋቾችም የበዓሉ አካል ለመኾን መዘጋጀታቸውን እና በዋዜማው በአደባባይ የጋራ ትርዒት እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል።
የበዓሉ ሥነ-ሥርዓት በሰላም ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሰቆጣ ከተማ ማኅበረሰብ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየፍቅር እና የተስፋ መግለጫው ‘አሱሪቲ’
Next articleየማይረሳው ቁስል