አካል ጉዳተኝነትን በጽናት ያሸነፈው የአሻግሬ ፈቃዴ የትንሣኤ መንገድ!

4
የዛሬው ባለታሪካችን ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘ ብርቱ ልጅ ነው። በልጅነቱ በደረሰበት የጤና እክል ምክንያት አካል ጉዳተኛ ኾኗል። ስሙ አሻግሬ ፈቃዴ ይባላል። በለጋነት ዕድሜው እንደ እኩዮቹ በትምህርት ቤት በመገኘት መማር እንዳልቻለ አጫውቶናል።
የትምህርት ዕድል አለማግኘቱ እና የገጠር ልጅ መኾኑ ግን ልመናን አማራጭ እንዲያደርግ እና እንዲሸነፍ አላደረገውም። ይልቁንም ራሱን በማጠንከር ተፈጥሮ የሰጠችውን ጸጋ መጠቀም እንደሚችል መንገድ አሳየችው እንጅ።
🔑 የአካል ጉዳተኝነት የሚያደርሰውን ፈተና በምን አሸነፈ?
በወጣትነቱ የባሕር ዛር ፍል (ችግኝ) እና ጌሾ በመሸጥ፤ ከጥለት ፎጣ እና ቆብ በመሥራት እና ለማኅበረሰቡ በመሸጥ የችግር መውጫ መፍትሔን ተጠቅሟል።
በራሱ ጥረት ለ27 ቀናት ፊደል በመቁጠር፤ አጻጻፍ እና ንባብን በመለማመድ በግሉ ጥረት ራሱን አስተምሯል።
🔑 ጥረት የወለደው የትንሣኤው ጅማሮ!
ከጥለት ክር የተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን በማምረት ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለቤት ኪራይ በመክፈል እና ቀለም በመግዛት የሥዕል ሥራን ጀምሯል።
በመጀመሪያው ወቅት ለሥዕል ሥራ ከሚያወጣው ወጭ በቅናሽ ዋጋ ሥዕሎቹን መሸጡን ያስታውሳል። አሁን ላይ በሥዕል ሥራ ውጤታማ በመኾን ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን ያነሳል።
በይበልጥ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎችን እንደሚስልም ተናግሯል። ከ1994 ጀምሮ የሥዕል ሥራ መጀመሩን ያነሳው ባለታሪካችን አሁን ላይ ለአራት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
ከሥዕል በሚያገኘው ገቢ የመኖሪያ ቤት ባለቤት እና ይበልጥ ተጠቃሚ መኾን እንደቻለም አንስቷል። ለሥራ ዕድል ለፈጠረላቸው ወጣቶች በወር እስከ 40 ሺህ ብር ደመወዝ እንደሚከፍልም ገልጿል።
ማንኛውም ሰው መሥራት እና መለወጥ እንደሚችልም ያምናል። አካል ጉዳተኝነት ለልመና ጎዳና ላይ የሚያስወጣ እና ተስፋ የሚያስቆርጥ ባለመኾኑ ራስን በማጠንከር፤ ለዓላማ በጽናት በመታገል ውጤታማ መኾን እንደሚገባ አመላክቷል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሕጋዊ የገቢ መሠብሠቢያ ኬላዎች የትኞቹ ናቸው?
Next articleየወቅቱ ፈተና!?