የሕገወጡ የሕወሃት ቡድን የታሪክ ማኅደር ሲገለጥ በ1960ዎቹ የትግሉን መነሻ ያደረገው በሀገር ውስጥ ከሚነቀሳቀሱ ከኦነግ እና ሌሎች ታጣቂዎች፤ ከሻዕቢያ እና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር መኾኑን ያሳያል።
የሀገሪቱን የሥልጣን ማማ ሲይዝ ግን ኤርትራን አሥገንጥሎ፤ ኢትዮጵያን ከባሕር በር አርቆ፤ የሀገር ውስጥ ታጣቂዎችን ደግሞ እንዲበታተኑ በማድረግ ሥልጣኑን በብቸኝነት መቆጣጠሩ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ ከአራት ኪሎ ወደ ደደቢት በርሃ የተጣለው ሕገወጡ ቡድን በቅርቡ ደግሞ ከተለያዩ ታጣቂዎች ጋር ጥምረት ፈጥሯል። ከታሪካዊ ጠላቶች እና ከሀገር ውስጥ ታጣቂዎች ጋር ያደረገው ጥምረት የጋራ ጠላት እንጅ የጋራ የሀገር ራዕይ እንደሌለው ቡድኑም ያውቀዋል።
ከሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ጋር በ1960ዎቹ መነሻ ላይ በጥምረት የታገለው እና ሕገ ወጡ ቡድን የሀገሪቱን ሥልጣን ሲቆጣጠር የበታተነው የኦነግ ሸኔ ቡድን ዛሬም አብሮት ተጣምሯል። ከዓመታት የታሪክ ስሕተቱ ትምህርት ባለመውሰዱ የኦሮሞ ሕዝብን ወደ ስቃይ ውስጥ ለማስገባት ጥምረቱን ተቀብሏል።
በሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ከኢትዮጵያ እንድትነጠል፤ በአምባገነን ሥርዓት እንድትመራ፤ ሕዝቧ በጭቆና እንዲኖር የተፈረደባት ኤርትራ ከቡድኑ ጋር ለበርካታ ዓመታት ጠላቶች ነበሩ። ዛሬ ላይ ደግሞ በአንድ ሊዋጉ ጥምረትን ፈጥረዋል።
ታዲያ ይህንን የከንቱ ምኞት ጥምረት ከልብ ላጤነው የጋራ ጠላት እንጅ የጋራ ሀገራዊ ራዕይ እንደሌላቸው ለመገንዘብ ቀላል ነው። ኢትዮጵያ ጸጋዋን እንዳትጠቀም፤ የኢኮኖሚ ዕድገቷ እንዳይረጋገጥ ማነቆ ለመፍጠር ከሚጥሩ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረትን በመፍጠር ሀገርን ለማፍረስ ሕገወጡ ሕወሃት እየሠራ ይገኛል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) የሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ከልብ የመነጨ የሰላም ፍላጎት የሌለው በመኾኑ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደ ጊዜ መግዣ መጠቀሙን ገልጸዋል።
መንግሥት ከስምምነቱ ማግሥት በጀት በመመደብ፤ ተቋርጠው የነበሩ መሠረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን በማስጀመር እና ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም ሰላምን ለማጽናት መሥራቱን ገልጸዋል።
የሕገወጡ ሕወሃት ቡድን በክልሉ መፈንቅለ መንግሥት በመፈጸም እና የጦርነት ቅስቀሳ በማድረግ የሰላም እፎይታን በአጭር መቅጨቱንም ተናግረዋል። ተጠያቂነትን በመፍራታቸው፤ የመገንጠል ዓላማን በመያዛቸው፤ በሥልጣን ላይ የዘረፉትን ሃብት ለማስቀጠል ባላቸው ፍላጎት መሠረት የፕሪቶሪያን ውል አፍርሰዋል ነው ያሉት።
ሕገወጡ ቡድን ሃብት የመሠብሠብ ፍላጎት እንጅ ሕዝባዊ የኾነ ሀገራዊ ዓላማ የለውም ብለዋል። ቡድኑ ከጥንት ጀምሮ በአዶሊስ፤ በጉንደት እና በጉራ ጦርነትን ገጥሞ የተሸነፈውን የግብጽ መንግሥት ፍላጎት ለማስፈጸም፤ ስልቱን ቀይሮ ከኤርትራ ጀርባ ካለው ግብጽ እና ከሻዕቢያ ታጣቂዎች ጋር ጽምዶ የሚል ጥምረትን ፈጥሯል ነው ያሉት።
ሻዕቢያ እና የሕገወጡ የሕወሃት ቡድን የግብጽን ዓላማ ለማስፈጸም እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመተባበር ሀገሩን እና መብቱን ሊያስከብር ይገባልም ነው ያሉት። የትግራይ ሕዝብ እናቶች ልጆቻችንን አትወስዱ፤ ለጦርነት የምንሰጠው ስንቅ የለንም በማለት፤ ወጣቶች ደግሞ አፈና ይብቃ እያሉ ሕገወጥ ቡድኑን እየተቃወሙ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
