
ተማሪ ዳዊት አማረ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ኩርባ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው: በ2018 የትምህርት ዘመን በክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና መቶ ከመቶ (100%) በማምጣት የላቀ ውጤት አስመዝግቧል።
ለስኬቱ ምስጢር የሆነው የጥናት ስልት ተማሪ ዳዊት ለዚህ ከፍተኛ ውጤት ያበቃው ጠንክሮ በማጥናቱ እንደኾነ ይናገራል። ተማሪው ከማታ ይልቅ በቀን የማጥናት ልምድ አለው። ውጤታማ ያደረገውን የጥናት መንገድ ሲያብራራ:-
”50 ደቂቃ ማንበብ፤ 10 ደቂቃ ማረፍ” የሚል ስልት እከተላለሁ። በዚህ ጊዜ አዕምሮዬ በየመካከሉ እያረፈ እና እየተዝናና እንደ አዲስ መረዳት እና ግንዛቤ የማዳበር አቅም ይጨምራል” ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርት በአግባቡ መከታተል፣ የማጣቀሻ መጽሐፍትን መጠቀም፣ የወላጆቹ እና የመምህራን ያልተለየ ድጋፍ ለውጤቱ መሠረት እንደኾኑ ገልጿል።
“ጥረት ካለ ውጤት አለ!” የሚል ጽኑ እምነት ያለው ዳዊት ማንኛውም ተማሪ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ካጠና ለላቀ ውጤት መብቃት እንደሚችል ተናግሯል።
የወደፊት ርዕይ ተማሪ ዳዊት ወደ ፊት ትምህርቱን በጥልቀት በመከታተል በኤሌክትሮ ማግኔቲዝም ፊዚክስ ዘርፍ ትልቅ ተመራማሪ የመኾን ሕልም አለው። ይህ ሕልም የመነጨው የኢትዮጵያ እናቶች በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት የሚያባክኑትን ጉልበት እና ስቃይ ለማስቀረት፣ ለሁሉም ነገር ወሳኝ የኾነውን የኤሌክትሪክ ኀይል ችግር ለመቅረፍ ካለው ጉጉት መኾኑን ገልጿል።
የወላጅ እና የመምህራን ድጋፍ የተማሪ ዳዊት አባት መምህር አማረ አለምዬ ልጃቸውንም ኾነ ሌሎች ተማሪዎችን ለከፍተኛ ውጤት ለማብቃት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ የዘወትር ተግባራቸው እንደኾነ ነግረውናል።
ለልጃቸው ዳዊትም የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት፣ በመምከር እና በማበረታታት ሁልጊዜም ከጎኑ እንደማይለዩ ነግረውናል።
ልጃቸው ምክራቸውን ሰምቶ እና ጠንክሮ አጥንቶ የተመኙትን የላቀ ውጤት በማግኘቱ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ገልጸዋል። በቀጣይም በአዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ እንዲማር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የተማሪ ዳዊት አማረን አስተማሪ የስኬት ጉዞ ለሌሎች ተማሪዎች እንዲደርስ ያጋሩ! ሀሳብዎንም በአስተያየት መስጫው ያካፍሉን።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
