“የዛሬ ሦስት ዓመት የተገዛልኝ ደብተር አሁንም ያለጥቅም እጄ ላይ አለ” ትምህርት አቋርጦ የቆየ ተማሪ

4
ግጭት ሕንጻዎችን እና መንገድን ብቻ አይደለም የሚያፈርሰው፤ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ሥነ-ልቦና ይሰብራል፤ ህልማቸውንም ያደበዝዛል።
በአማራ ክልል ላለፉት ሦሥት ዓመታት በቆየው የሰላም እጦት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት እና ወጣቶች ከዕውቀት ማዕድ ተገፍተዋል።
የትምህርት ቤቶች የደወል ድምጽ ተቋርጠዋል፤ ጥቁር ሰሌዳዎች እና መቀመጫ ወንበሮች በከባድ አቧራ ተሸፍነዋል። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ይባስ ብሎ ወድመዋል።
ምሁራን እንደሚሉት ሦሥት ዓመት ሙሉ ትምህርት ቤት መዝጋት ማለት ነገ ሳይንቲስት፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር እና መምህር ከሚኾኑ ታዳጊዎች ላይ ዕድሜ መቀነስ ነው።
መጭው መስከረም ወር ለብዙዎች አዲስ ተስፋ ይሁን እንጅ በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ለሚኖሩት ተማሪ ሐብታሙ አስቻለው እና ሙሉጌታ አበበ ግን ከተስፋ በላይ ነው።
ባለፉት ሦሥት ዓመታት በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ተለይቶ መቆየቱን ተማሪ ሀብታሙ ነግሮናል።
እኩዮቹ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ለመኾን ሲዘጋጁ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የኾነው ሐብታሙ ግን በሰላም እጦት ምክንያት ዕድሜው እና ህልሙ አብሮ እየባከነ መኾኑን በቁጭት ይናገራል።
“ዘንድሮ ሰላም ከኾነ ለመማር ዝግጁ ነኝ፤ ትምህርት ናፍቆኛል፤ ትምህርት ቤት በተከፈተ እንጂ ደብተርም አሟልቻለሁ፤ የዛሬ ሦሥት ዓመት የተገዛልኝ ደብተር አሁንም እጄ ላይ አለ” ይላል።
ይህ ንግግር የቁሳቁስ መሟላት ማሳያ ሳይኾን፣ የአንድ ብሩህ ሕጻን ለትምህርት ያለው ጥልቅ ፍላጎት እና የትውልድ ስብራትን የሚያሳይ ነው። የብዙ ወላጆችን አንጀት የሚበላ እና የትምህርትን ዋጋ የሚያውቅ ሰው ልብ የሚነካ የቁስል ድምጽ እንጂ።
ሌላኘው ተማሪ ሙሉጌታ አበበ በበኩሉ በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ርቆ መቆየቱን ነው የነገረን።
ተማሪ ሙሉጌታ እንደገለጸው በአካባቢያቸው በሚሰማው የጥይት እና የቦምብ ድምጽ በበርካታ ሕጻናት አዕምሮ ውስጥ ከባድ የሥነ-ልቦና ስብራትን ጥሏል፤ በርካቶች ለሱስ እና ያለዕድሜ ጋብቻ ተጋልጠዋል፤ ለጉልበት ብዝበዛም ተዳርገዋል፤ የነገ ሕልማቸውን አጥተው ለጭንቀት ተጋልጠዋል።
ተማሪ ሙሉጌታ ሁልጊዜም ቢኾን ተምሮ ትልቅ ደረጃ የመድረስ እና በጤናው ዘርፍ ማኅበረሰቡን የማገልገል ትልቅ ህልም እንዳለው አጫውቶናል።
ተማሪዎቹ ትምህርት ቤት ይከፈት እንጅ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል የትምህርት ቁሳቁስ አሟልተናል፤ በሥነ ልቦናም ተዘጋጅተና ነው ያሉት።
ምንም እንኳን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በመጭው የ2019 የትምህርት ዘመን ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እና መስከረም 5/2019 ዓ.ም ትምህርት ለመጀመር ማቀዱን ቢገልጽም እንደ ሐብታሙ ላሉ ተማሪዎች ግን በተግባር የሚረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ያስፈልጋል።
ትምህርት ቤቶች የሰላም ቀጣና እንዲኾኑ ማድረግ እና የልጆችን የመማር መብት ማስከበር የሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ኀላፊነት እና የሞራል ግዴታ ሊኾን ይገባል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleስሙን የወረስሽ፣ ግብሩን የጠበቅሽ – ደብረ ታቦር
Next articleበ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መቶ በመቶ ያመጣው ባለ ምጡቅ አዕምሮ