
ብርሃን የበራበትን፤ መለኮት የተገለጠበትን፤ ምስጢር የተመሰጠረበትን ተራራ በአምሳሉ የተሰጠሽ፤ ለክብሩ መገለጫ የታደልሽ፤ ስሙን የወረስሽ፤ ግብሩን የጠበቅሽ፤ የትናንቱን ያጸናሽ፤ የዛሬውን የዋጀሽ፤ የነገውን ዛሬ ላይ ያበጃጀሽ ጥንታዊት ነሽ።
በታቦር ላይ የኾነውን ሥርዓት ትፈጽሚያለሽ፤ የጌታን ክብር ትገልጫለሽ፤ በዚያ ተራራ ላይ የተፈጸመውን የረቀቀ ምስጢር ለሕዝብ ሁሉ ትነግሪያለሽ፤ ለትውልድ ሁሉ ትገልጪያለሽ።
አንቺ የቤተ መንግሥቱን ሥርዓት፣ የቤተ ክህነቱን ምልዓት አላጎደልሽም፤ ሁሉንም በአይነቱ ትፈጽሚያለሽ፤ ትናንት የነበረውን ዛሬም ታሳያለሽ፣ ለነገም ትጠብቂያለሽ እንጂ ትናንትን አትረሽም፤ የአባቶችሽን ታሪክ አትዘነጊም፤ የከበረውን ታሪክ እና ሃይማኖት አትተይም።
አንቺ አምላክ ለመመስገኛ የፈጠረሽ፤ ለክብሩ መነገሪያ ያበጃጀሽ፤ ከጥንት ጀምሮ በጥበብ የጠበቀሽ፤ ዘመን በደረሰ ጊዜ የገለጠሽ፤ ከፍ ከፍም ያደረገሽ፤ ከተራራው የገዘፈ ግርማ እና ሞገስ ያደለሽ ነሽ ደብረ ታቦር።
ደብረ ታቦር ስሟን የወረሰችው ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ከገለጠበት ከታቦር ተረራ ነው። አጼ ሠይፈ አርድ ወደ ኢየሩሳሌም አቅንተው ነበር። በዚያም ቆይተው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ። በሀገራቸው አውራጃዎችን እየተዘዋወሩ ያያሉ። የአሁኑ ደብረ ታቦር አካባቢ በደረሱ ጊዜም በኢየሩሳሌም ያዩትን ተራራ ተመለከቱ። ይህስ በኢየሩሳሌም ያየሁትን የታቦርን ተራራ ይመስላል አሉ። ሥፍራውንም ደብረ ታቦር አሉት።
ይህች ብርሃነ መለኮት ከተገለጠበት ተራራ ላይ ስም የወረሰች ከተማ ደብረ ታቦር በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄ) በድምቀት ታከብራለች።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌትነቱን ሥራ ከፈጸመባቸው ዘጠኝ አበይት በዓላት መካከል አንደኛው ነው፤ ሌሎቹ በዓላት ድርጊቱ በተፈጸመበት ሥራ ስማቸው ይጠራል፤ ደብረ ታቦር ግን ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ የሚጠራ በዓል ነው ይላሉ።
ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን እና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ። ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ። ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም ሙሴ እና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።
እርሱም ገና ሲናገር እነኾ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነኾም ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው ተብሎ እንደተጻፈ ደብረ ታቦር ታላቅ ምስጢር የተገለጠበት በዓል ነው።
በዓለ ደብረ ታቦር በብሉይ ኪዳይ ትንቢት የተነገረለት፤ በሐዲስ ኪዳንም በተግባር የተፈጸመበት ታላቅ በዓል ነው ይላሉ ሊቁ። ይህ ሥፍራ ተስፋ የተፈጸመበት ነው፤ ዲያቢሎስም ድል የተነሳበት ነው።
ክርስቶስ ትንቢት የተናገሩ ነብያትን፣ ትንቢት ሲጠባበቁ የነበሩ ሐዋርያትን በአንድ ላይ አድርጎ ያገናኘበት፣ ሙሴን ከመቃብር፣ ኤሊያስንም ከብሔረ ሔዋን የጠራበት ነው ትላሉ። ደብረ ታቦር ሲባል ተራራው ነው፤ እኛም በተራራው ላይ የተፈጸውም ምስጢር እናከብርበራተለን ነው የሚሉት።
በዓለ ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ የታየበት፣ ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው ይላሉ። በዚያች እለት ደመና በብርሃን ተመላች፤ ምድርም በነጎድጓድ ተናወጸች። የደብረ ታቦር ተራራ በብርሃን ተመልቷልና፤ እረኞች መምሸቱን አላወቁም ነበር። ቀን መስሏቸው በዚያው ነበሩ። ወላጆቻቸውም ልጆቻቸውን የት ገቡ እያሉ ችቦ እያበሩ፣ ለልጆቻቸው ሙልሙል ይዘው ተጓዙ። ይህም ሥርዓት ዛሬ ድረስ ይደረጋል።
ደብረ ታቦር ለቤተክርስቲያን ታላቅ መሠረት ነው ይላሉ ሊቁ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይህን በዓል ለትውልድ እየነገረች በድምቀት ታከብረዋለች። ልጆች ጅራፍ ያጮኻሉ፣ ይህ በደብረ ታቦር የተሰማው ነጎድጓድ ምሳሌ ነው፤ ቡሄ እያሉ ያዜማሉ ብርሃኑን ይነገራሉ፤ አምላክነቱን ይመሰክራሉ፤ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ሃይማኖቱን ባሕል አድርገው በሕጻናቱ ልብ ላይ ዘርተውታል፤ ሊዚያም ነው በኢትዮጵያ ላይ ልዩ ኾኖ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚከበረው ይላሉ።
በዓለ ደብረ ታቦር በደብረ ታቦር ደግሞ የተለየ ነው የሚሉት ሊቁ ስለ ምን ቢሉ ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ያለበት ተራራ የእስራኤሉን ይመስላልና። ደብረ ታቦር እና ደብረ ታቦር፣ ጉና እና አርሞኒዬም ተመሳሳይ ናቸው ነው የሚሉት። የእስራኤሉ ደብረ ታቦር ለምለም ነው፤ ይሄኛው ደብረ ታቦርም ለምለም ነው፤ ከዚያኛው ደብረታቦር ላይ ተሁኖ ዮርዳኖስ ይታያል፤ ከዚህኛው ደብረታቦር ላይ ተሁኖ ጣና ይታያል፤ ከዚያኛው ደብረ ታቦር ላይ ተሁኖ ኢየሩሳሌም በሙሉ ትታያለች፤ ከዚህኛው ደብረታቦር ላይም ተሁኖ ደብረ ታቦር ከተማ እና የዓይን ብርሃን ማየት እስከሚችለው ድረስ ያለው ይታያል ይላሉ።
ደብረ ታቦር በኢትዮጵያ ብቸኛው የተክሌ አቋቋም ማስመስከሪያ የሚገኝባት ታሪክን ከሃይማኖት፣ ባሕልን ከእሴት፣ ጀግንነትን ከብልሃት አጣምራ የያዘች፣ አክብራ የጠበቀች፣ ጠበቃ ለትውልድ ያሻገረች ጥንታዊት እና ታሪካዊት ናት። ይህች ጥንታዊት ከተማ በዓለ ደብረ ታቦርን ከአበው በተቀበለችው ሥርዓት መሠረት አድምቃ ስታከብር ኖራለች፤ እነኾ ዛሬም አክብራለች፣ ወደፊትም ታከብራለች።
በበዓለ ደብረ ታቦር የተክሌ አቋቋሙ የሚቆሙ ሊቃውንት የሰማይ መላዕክት ይመስላሉ፤ ያያቸውን ሁሉ ያሳሳሉ፤ ያስደንቃሉም።
በደብረ ታቦር በዓለ ደብረ ታቦር ሲከበር የቤተ መንግሥቱም፣ የቤተ ክህነቱም ሰዎች በአንድነት ይሰባሰባሉ፤ ሊቃውንት የከበረውን ሥርዓት ይፈጽማሉ፤ ሕጻናቱ ቡሄ እያሉ አምለካቸውን ያመሰግናሉ፤ የታቦር ተራራ ጸዓዳ በለቡ ምዕምናን ትጨነቃለች፤ ከአፍ እስከ ገደፏ መልታ ለአምላኳ ምስጋና ታቀርባለች፤ በውዳሴ ታረግዳለች።
በዚህች ቀን በደብረ ታቦር የተገኘ ሰው ምንኛ የታደለ ነው ይላሉ ሊቁ። ስለ ምን ቢሉ ድንቅ ሥርዓት ይፈጸምባታል፤ ከአበው የቆዬው ምስጢር እና ሥርዓት ሳይበረዝ ይታይባታልና ይላሉ።
የምሥጢር መገለጫዋ፣ የብርሃን መታየዋ ደብረ ታቦር ታሪክን ትናገራለች፤ ሃይማኖትን ትሰብካለች፤ ሥርዓትን ታጸናለች፤ ባሕል እና እሴትን እስከ ክብሩ ትጠብቃለች።
#አሚኮ #በዓለ_ደብረ_ታቦር #ቡሄ #ደብረ_ታቦር #አሚኮ
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_13_2018_ዓ_ም
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
