
ባለፉት ሦሥት ዓመታት በአማራ ክልል ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ እና አለመረጋጋት ምክንያት ሰፊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ደርሷል። የዚህ ችግር ሰለባ ከኾኑት የክልሉ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ጎጃም ዞን አንደኛው ነው።
በዞኑ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች አገልግሎት በማቋረጣቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ከርመዋል፤ ሕክምና የማግኘት መብታቸውም ተገድቧል።
በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ዜጎች በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት እና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን የማስቀጠል መብታቸው ተገድቦ እንደነበር የዞኑ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በትራንስፖርት እና የመንገድ መዘጋት ምክንያት ምርት እና አገልግሎትን ለገበያ ለማቅረብ ተቸግረው እንደነበር አንስተዋል። ይህም የአርሶ አደሮችን እና የነጋዴዎችን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል።
ንጹሐን በግፍ ግድያ፣ እስራት እና እገታ ሰለባ ኾነዋል፤ ነዋሪዎችም ሕክምና ለመሄድ እና በሞት የተለዩ ወገኖቻቸውን በክብር ለመቅበር እንኳን ተስፋ እስከ መቁረጥ ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በዞኑ ከበፊቱ የተሻለ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ ይገኛል ብለዋል። ተቆልፈው የነበሩ የትምህርት እና የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ የተረጋጋ የሰላም ሁኔታ በመኖሩም በዞኑ የማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ከበፊቱ መሻሻሉን ተናግረዋል።
መንግሥት አሁን የታየውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ለታጣቂዎች የዘረጋውን የሰላም በር ክፍት አድርጎ በትኩረት እንዲሠራ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ የዞኑ ማኅበረሰብ ላለፉት ሦሥት ዓመታት ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳርጎ መቆየቱን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የዞኑ ማኅበረሰብ ከበፊቱ የተሻለ “አንጻራዊ ሰላም” እያገኘ ይገኛል ብለዋል።
ላለፉት ሦሥት ዓመታት ተቆልፈው የነበሩ ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ የመማር ማስተማር ሥራ ጀምረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የጸጥታ ችግሩን በመቋቋም በገጠሩ አካባቢ የመብራት ዝርጋታ፣ የመንገድ ግንባታ እና የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
ፍኖተ ሰላም ከተማን ጨምሮ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች የንግድ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው መነቃቃት አሳይቷል።
“የወገናችን ስቃይ ይብቃ!” በማለት በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው እየገቡ ነው። ትግሉ ዓላማ ቢስ እና እርስ በርስ የመጠፋፋት መኾኑን የተረዱ ወጣቶች በራሳቸው ወደ ቀያቸው ተመልሰው ልማት ላይ ተሰማርተዋል ብለዋል።
የዞኑ ማኅበረሰብ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው እንዲገቡ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ተገልጿል።
የዞኑ አሥተዳደር የ2019 በጀት ዓመት ዋና ትኩረቱ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ ጫካ ያሉትን ታጣቂ ኀይሎች በሰላም መመለስ እና የሕዝቡን ደኅንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደኾነ አስታውቀዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የታየው አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲቀየር የማኅበረሰቡ፣ የወጣቶች እና የመንግሥት ድርሻ ምን መኾን አለበት? ሃሳብዎን በኮሜንት ያካፍሉን?
#አሚኮ #ሰላም #ልማት #ምዕራብጎጃም #አማራክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_08_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
