“ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሠራል” ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ

3

 

የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን በ2018 በጀት ዓመት በሕግ ማስከበር ሥራ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ እና የጸጥታ ኃይሉን እየመሩ ለሚገኙ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ መምሪያዎች እውቅና ሰጥቷል።

የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ ውይይት ለቀናት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ክፍተቶችን በመለየት እና የቅንጅት ሥራዎችን በመገምገም በቀጣይ ስኬታማ ተግባራትን ለማከናወን ሰፊ ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት። በክልሉ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት እና ዕድገት በጸጥታ ኃይሉ መስዋዕትነት የመጣ መኾኑን ተናግረዋል።

የሚሊሻ ኃይሉ ከሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በጥምረት በመኾን ቀበሌዎች፤ ወረዳዎች እና ዞኖች ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር በቁርጠኝነት ሠርቷል ብለዋል።

እውቅና የተሠጣቸው መምሪያዎች በአካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን የቻሉ መኾናቸውን ተናግረዋል። የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ፤
የኢኮኖሚ ልማት እንዲሳለጥ፤ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ እና ማኅበረሰቡ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ የጸጥታ ኃይሉ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አንስተዋል።

ሁሉም ቀበሌዎች የመንግሥት አገልግሎትን እንዲሠጡ እና አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ የሰላም እንዲሸጋገር በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ ድጋፍ በማድረግ እና መረጃ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።

#አሚኮ #peace #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_08_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“በቀዳማይ ልጅነት ጊዜ ላይ መሥራት የነገዋን ኢትዮጵያ በጠንካራ መሠረት ላይ መሥራት ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)