
በባሕር ዳር ከተማ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች ምልከታ ተካሂዷል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ከጽንስ እስከ ስድስት ዓመት ባለው የቀዳማይ ልጅነት ጊዜ ላይ መሥራት የመንግሥት የሰው ሃብት ልማት ሥራዎች ዋነኛ አካል ነው ብለዋል።
በዚህም መሠረት የሕጻናት ዕድገት እና እንክብካቤ ከእናቶች ማሕጸን ጀምሮ ጤናቸውን፣ የአዕምሮ እና የአካል ዕድገታቸውን በቅርበት በመከታተል ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የሕጻናት ማቆያ እና የትምህርት ማዕከላት የልጆችን ሁለንተናዊ ዕድገት በሚያግዙ የቤት ውስጥ እና የቤት ውጭ ጨዋታዎች የተሟሉ መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሕጻናት ወደ መደበኛ ትምህርት ከመግባታቸው በፊት ራሳቸውን፣ አካባቢያቸውን እና ማኅበረሰባቸውን በሚገባ እንዲያውቁ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የቀዳማይ ልጅነትን ሀገራዊ ራዕይ ከግብ ለማድረስ አሁን ያለውን ቅንጅታዊ አካሄድ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራሞች በፍጥነት እየተስፋፉ ነው ብለዋል። አሁን ያለውን ተደራሽነት ለማስፋትም በ85 ከተማ አሥተዳደሮች ተግባራዊ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
በቀዳማይ ልጅነት ጊዜ ላይ በጥራት እና በትኩረት መሥራት የነገዋን ኢትዮጵያ ጠንካራ ለማድረግ እና አርቆ አሳቢ ትውልድ ለመቅረጽ መሠረት መኾኑን አስገንዝበዋል። ይህንንም ሀገር ገንቢ ተግባር ለማገዝ ሚዲያው ስለ ሕጻናት እንክብካቤ እና ዕድገት በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጥር ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የቀዳማይ ልጅነት ልማት የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። የመንግሥት ሠራተኛ እናቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ኾነው ልጆቻቸውን በሰዓቱ ማጥባት እና መመገብ እንዲችሉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት እንዲኖሩ እየተደረገ ይገኛል።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ነባር ማቆያዎች በተለይም ከውጭ መጫወቻ ስፋት እና ምቾት አንጻር የተፈለገውን ደረጃ የጠበቁ እንዳልኾኑ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ደረጃ የማሻሻል እና አዳዲስ ደረጃቸውን የጠበቁ ማቆያዎችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።
ከከተማ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር 234 የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎችን በዚህ ዓመት ለመገንባትም ታቅዷል።
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ማዕከል ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ መሠረት ዘላለም (ዶ.ር) በአማራ ክልል የሚገኘውን የቀዳማይ ልጅነት ልማት ጅምር አድንቀዋል። በተለይም በሀገር በቀል መጫወቻዎች የታገዘ ትምህርት መሰጠቱ እና የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት መከፈታቸው የትውልድ ግንባታ ላይ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የጤና፣ የትምህርት እና የማኅበረሰቡ ጠንካራ ቅንጅት ተስፋ ሰጭ ጅምሮች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ይህን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ሌሎች ክልሎችም ከዚህ ምርጥ ተሞክሮ በመማር ለትውልድ ግንባታ በትኩረት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
#አሚኮ #ቀዳማይልጅነት #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_08_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
