
የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ ለሀገር እና ለአካባቢው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኝ የቱሪዝም ሀብት ነው።
በዓሉን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅም በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ የፎክሎር ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በሁሉም የዋግ ኽምራ አካባቢዎች የሚከበረውን የሻደይ ጨዋታ አስመልክተው በሥነ-ቃሉ እና ዜማው ላይ ጥናት ያቀረቡት የፎክሎር ባለሙያው እሸቱ ታደሰ በዓሉ ለዋግ ልጃገረዶች የነፃነት እና የደስታ መግለጫ ብቻ ሳይኾን ማንነታቸው የተገነባበት መኾኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ሻደይን ከቱሪዝም ፋይዳው አንጻር ያጠኑት አቶ መላኩ አሻግሬ በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል የቱሪስት መዳረሻ መኾኑን ጠቁመዋል።
ምሁራንም የበዓሉን ዜማ፣ ሥነ-ቃል፣ አለባበስ እና ሌሎች ባሕላዊ እሴቶች በመመርመር ለዓለም የማሳወቅ ኀላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ይርጋ ማርዬ የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታን ሳይበረዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ አጥኝዎች የምርምር ግኝቶቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ እንደሚመቻች ተናግረዋል።
ወልድያ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች በዋግ ባሕላዊ ጨዋታዎች ዙሪያ የጀመሯቸው ጥናት እና ምርምሮች የሚበረታቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም መምሪያቸው በዘርፉ ለሚሰማሩ ተመራማሪዎች ሙሉ እገዛ የሚያደርግ መኾኑን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
