በኪራይ የሚተነፍሰው የሀገር ሳምባ – ወደብ አልባነት እና የኢትዮጵያ ጥያቄ

10
🌌የጂኦግራፊ እጣ-ፈንታ የሀገርን ታሪክ፣ ኢኮኖሚ እና የሕልውና ትርታ የሚወስን የማይፋቅ ማህተም ነው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት ታሪክ ከ1983ቱ የፖለቲካ ንፋስ ጋር ተያይዞ የተቀነጠሰ የሀገር የደም ስር እንደኾነ “የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ከጎረቤቶቿ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተሠራው ጥናት አረጋግጧል።
የወቅቱ የፖለቲካ አመራር የውቅያኖስን ስትራቴጂካዊ ጥልቀት በገበያ ሸቀጥ ስሌት ተክቶ አቅም ሲኖር በገንዘብ እንደሚገዛ ዕቃ ያቀለለበት ያ ታሪካዊ ስህተት ዛሬ ላይ ሀገሪቱን በጂኦ-ፖለቲካዊ የውኃ ጥም እንድትሰቃይ ማድረጉን ጥናቱ ይጠቅሳል። ይህ ውሳኔ የሀገርን የተፈጥሮ መተንፈሻን ቆርጦ ለባዕድ ከመስጠት ያልተናነሰ፣ የሀገርን ሉዓላዊ አቅም በጎረቤቶች በጎ ፈቃድ ላይ ያንጠለጠለ አሳዛኝ የፖለቲካ ክሽፈት ተደርጎ ተወስዷል።
የባሕር በር አልባነቱ ያስከተለው የኢኮኖሚ ኪሳራ በቁጥር ከሚገለጸው በላይ እጅግ የረቀቀ እና የሕዝብን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያደማ ነው። በመሠረቱ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መኾኗ በኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ “አንድ እርምጃ ወደ ፊት፣ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ” እንደሚባለው ዓይነት እንደኾነባት ይኸው ጥናት ጠቁሟል።
ሀገሪቱ ከተለያዩ የኤክስፖርት ዘርፎች የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እና ለወደብ አገልግሎት በምታወጣው ከፍተኛ ወጭ መካከል ያለው አለመመጣጠን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ስጋት ኾኖ ይነሳል። ጥናቱ እንዳረጋገጠው ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የወደብ ኪራይ (አብዛኛውን ለጂቡቲ) ትገብራለች። ይህ ወጭ በ2015 እ.ኤ.አ. ብቻ የሀገሪቱን ዓመታዊ በጀት ሩብ የሚሸፍን እንደነበርም አመላክቷል።
ጥናቱ የባሕር በር አልባነት ኢትዮጵያን ምን ያህል እንደፈተናት ለማሳየት አብነት ያነሳው ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱ በአማካይ በዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ መክፈሏን ነው። በዘህም ስሌት መሠረት እስከ 2024 እ.ኤ.አ ያለው አጠቃላይ የወደብ ወጭ ወደ 27 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።
በባዶ ሜዳ የሚፈሰው ይህ የሀገር ደም 5 ቢሊዮን ዶላር የፈጀውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ወደ ስድስት ጊዜ መገንባት የሚያስችል ግዙፍ አቅም ነው ሲል ጥናቱ ተንትኗል። ይህ የባሕር በር በማጣት ብቻ የምትቀጣው “የጂኦግራፊ ግብር” መገንባት የነበረባቸውን ትምህርት ቤቶች፣ ማከም የነበረባቸውን ሆስፒታሎች እና መቀየር የነበረበትን የዜጎች ሕይወት በውቅያኖስ ሞገድ አሟምቶ አስቀርቶታል።
ዓለም አቀፍ ምሁራን እንደሚያስረዱት ወደብ አልባነት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ከባሕር ርቀት፣ ከተጓታች ቢሮክራሲ፣ ከኢንሹራንስ መናር እና ከመሠረተ ልማት ውስንነት ጋር ተዳምሮ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያቀጭጭ ከባድ መዋቅራዊ ማነቆ ነው።
ከኢኮኖሚው አረንቋ ባሻገር ወደብ አልባነት የሚያስከትለው የፖለቲካ እና የደኅንነት ስጋትም የሀገርን የጀርባ አጥንት የሚያላላ ነው። የባሕር በር አለመኖር በተለይ ደካማ እና ያልተረጋጉ ጎረቤቶች ባሉበት ቀጣና ውስጥ ሀገሪቱን ከባሕር ለሚመነጩ የደኅንነት ማዕበሎች በቀላሉ ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችልም ይታመናል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገችው ያለው የዲፕሎማሲ ንግግር የቅንጦት ፍላጎት ሳይኾን የታነቀውን የሕልውና ትንፋሽ የማስለቀቅ የሞት እና የሽረት ትግል ነው። የተቆረጠውን የውኃ እምብርት መልሶ ለመቀጠል የሚደረጉ ጥረቶች ሀገሪቱ ከታሰረችበት የጂኦ-ፖለቲካዊ አዙሪት ወጥታ የነገዋን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስፈልግ ታሪካዊ ግዴታ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የባሕር በር ጉዳይ በማያሻማ ሁኔታ “የሕልውና ጉዳይ” በማለት ገልጸውታል። የባሕር በር ጥያቄ ከጦርነት እና ከግጭት ፍላጎት የሚመነጭ ሳይኾን በፍጥነት እያደገ ላለው እና ከ130 ሚሊዮን በላይ እንደኾነ ለሚነገረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕጋዊ የመተንፈሻ ፍላጎት መኾኑን በማስመርም በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
“በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ መኖር አንችልም፤ የውኃ ጥማችንን በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰላማዊ ድርድር መፍታት አለብን” በማለትም የባሕር በር የቅንጦት ሳይኾን የኢትዮጵያ የመኖር እና ያለመኖር ውሳኔ መኾኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ከተጣለባት የጂኦግራፊ ግብር ተላቃ አዲሱን የብልጽግና ምዕራፍ በፍትሐዊ የሀብት ትስስር፣ በንግድ እና በሰላማዊ ድርድር ለመክፈት ያላትን ጽኑ ሀገራዊ አቋም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ደብተር ድጋፍ ያደረገው ተቋም
Next articleየሻደይ ባሕላዊ ጨዋታን የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ ይገባል።