የ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ደብተር ድጋፍ ያደረገው ተቋም

8
📚
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ “አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት ቁሳቁስ የማሠባሠቢያ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የኾኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ እና የሕጻናትን ችግር ለመፍታት የሁሉም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ የሚያስፈልግ በመኾኑ መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ዩኒፎርም ሳይለብሱ፣ ደብተር እና እስክርቢቶ ሳይዙ ብሎም ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ አፍረው ከጓደኞቻቸው ተለይተው የሚመለሱ ልጆች በርካታ ናቸው ብለዋል።
ዩኒፎርም እና ደብተር መግዛት የማይችሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ፈተና ኾኖባቸዋል። ይህ መርሐግብርም ችግር ያለባቸውን ልጆች ችግራቸውን የሚፈታ ነው ብለዋል።
ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ገበታ ለማስገባት የመጀመሪያው የሚያስፈልገው የትምህርት ቁሳቁስ ነው። ይህም አንዱ የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ የመጀመሪያው የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ነው።
በወቅታዊ ችግሩ ምክንያት በርካታ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እና በኢኮኖሚ እጥረት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ የሚቸገር ማኅበረሰብ ብዙ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የክልሉ ማኅበረሰብ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ባንኮች፣ ግለሰቦች እና ሌሎችም ይህንን በጎ አድራጎት ተግባር በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
መርሐግብሩ በክልል ብቻ የሚቆም ሳይኾን እስከ ቀበሌ ድርስ ተደራሽ ይደረጋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ይህም በ2019 የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ቤት ለሚመለሱ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ ሁሉም ለድጋፉ እጁን እንዲዘረጋ አሳስበዋል። “ልጆቻችን እኛ እያለን ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾን የለባቸውም” ማለት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የዓባይ ህትመት እና ወረቀት ፖኬጂንግ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ነጋ ይሁኔ ታዳጊዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ በየ ዓመቱ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት 60 ሺህ ደብተር ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ድጋፉ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት እንደሚያግዝም ነው የገለጹት። ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የመምህራን ማኅበር ምክትል ኘሬዝዳንት እናውጋው ደርሰህ ማኅበሩ 24 ደርዘን ደብተር በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። በተዘጋጀው መርሐግብር ብቻም ሳይኾን ሁልጊዜም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደርጉ መኾኑንም አንስተዋል። ድጋፉ የሕጻናትን ሥነ ልቦና ይገነባል፤ የሕሊና እርካታ የሚሰጥ በጎ ተግባርም ነው ብለዋል።
መርሐግብሩ ከነሐሴ 13/2018 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
#AmharaEducationBureau#NoChildOutOfSchool
#EducationForAll#SupportOurStudents
ዘጋቢ: ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአዳሪ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ጥራት ያላቸው ዋጋ ከፍ ያለ ነው።
Next articleበኪራይ የሚተነፍሰው የሀገር ሳምባ – ወደብ አልባነት እና የኢትዮጵያ ጥያቄ