መተጫጫ እና የከንፈር ወዳጅ መገናኘው እንግጫ ነቀላ

11
አንተ ከንፈር ወዳጅ፣ በጊዜ ሳመኝ
ጤፍ አበጥራለሁ፣ የሰው ግዙ ነኝ
እንግጫዬ ሰሌን ሳልደቁሰው ኩሌን …
እንግጫዬ ደነፋ ጋሻውን ደፋ፤ እየተባለ
የክረምቱ ዘመን ማብቃያ እና የአዲስ ዓመት ብስራት የኾነውን “እንግጫ ነቀላ እና ከሰይ አጨዳ” በጎጃም ምድር በነሐሴ ወር መገባደጃ ላይ በድምቀት እና በታላቅ ቱፊት ይከበራል ።
ይህ በዓል መሬት ከጭጋግ እና ከጨለማው ዘመን ወጥታ በልምላሜ እና በአደይ አበባ የምታጌጥበት፣ ወጣቶች እና ልጃገረዶችም ባሕላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁበት የነፃነት እና የደስታ ቀን ነው።
​የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዋ ቀረዓለም ዘውዱ የእንግጫ ነቀላ እና ከሰይ አጨዳ የልጃ ገረዶች የነፃነት ቀን መኾኑን ትገልጻለች። በዓሉ ከመድረሱ በፊት ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች ልዩ ዝግጅቶችን እንደሚያደርጉም ተናገራለች።
በዋዜማው ያላገቡ ልጃገረዶች ከፈትል እና ከጥልፍ የተሠሩ ነጭ ቀሚሶችን ይለብሳሉ። ፀጉራቸውን የተለየ ሹሩባ ይሠራሉ። በተለይም ያላገቡ ልጃ ገረጆች በላይነሽ መስቀል ከአንገታቸው ያደርጋሉ። ከወገባቸው ደግሞ ምሪ እንደሚያደርጉ ነው የተናገረችው።
ከቆዳ የተለበጡ ከበሮዎችን በመያዝ አምረው እና ደምቀው ወደ ሜዳ ወይም እንግጫ ወደ አለበት መስክ ይዘምታሉ።
ወጣት ወንዶች ደግሞ ጎን ለጎን ችቦ ያዘጋጃሉ። ከሴቶች ጋር በቅኝት እና በፉክክር ዜማዎችን ይሳተፋሉ። ልጃገረዶች በሰፈር ተጠራርተው ከሌሎች ሰፈሮች ቀድመው እንግጫ ለመንቀል በሽቅድድም ወደ ሜዳ እንደሚወጡ ተናገራለች። በጉዞው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ልጃገረዶች ያዜማሉ ሲሄዱ ወደ እንግጫ ነቀላ።
​እንግጫችን የወሩ፣ የቦረቦሩ…
እንግጫችን ዋይ ዋይ፣ አበበ ወይ
እንግጫዬ ነው ብዬ፣ ጤፍ አረም ውዬ… ሲሉ ያዜማሉ።
ከእንግጫ ነቀላው እና ከሴ አጨዳው ሲመለሱ ደግሞ
“እቴ አበባ ነሽ ወይ
አበባም ያብባል፣ በየሁሉም ደጂ፣
ምነው የኔ የለም፣ የከንፈር ወዳጂ፣
አንተ ከንፈር ወዳጅ፣ በጊዜ ሳመኝ፣
ጤፍ አበጥራለሁ፣ የሰው ግዙ ነኝ…”
እያሉ እንደሚያዜሙ ነው የምትገልጸው።
ወንዶች የሚወዷቸውን ልጃገረዶች እያሯሯጡ ለመሳም ወይም አንገታቸው ላይ መስቀል ለማሰር ይሞክራሉ፤ ሴቶቹም እንደ ምርጫቸው ይቀበሏቸዋል ወይም ይቃወሟቸዋል።
ለወንዶች ልጃ ገረዶች እንዲህ እያሉ ያዜማሉ ነው የምትለው።
ተው አብራልኝ ዳቦት፣ በናትህ ሞት
አበራህልኝ ወይ ወንድሜ ሆይ
ሊያበራልኝ ተነሳ ወንድም ጎልሳ እያሉ ያዜማሉ።
ከዚያም ወንዶች እያሯሯጡ የሚፈልጓትን ይስማሉ ወይም የአንገት መሥቀል ያደርጋሉ ትላለች። አንዷን ልጃ ገረድ ብዙ ወንዶች የሚፈልጓት ከኾነ በትግል ጨዋታ ያሸነፈ ይስማታል ያለችው ቀረዓለም ዘውዱ ልጃ ገረዷ የማትፈልገው ከኾነ አትሳምም ነው ያለችው።
ከሜዳ የተነቀለው እንግጫ ይሸረባል። ከዚያም በጥዋት ተነስተው የተሸረበውን እንግጫ በሰፈር በመዞር ከትልቅ ሰው ቤት በመጀመር “እንኳን አደረሳችሁ”እያልን እናደርሳለን ብላለች። ቤተሰቦችም መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ ነው ያለችው።
ትልልቅ ሰዎችም ምርቃን ይመርቃሉ ዓመት ያደርሰን ይላሉ። አብረው በመጫወት እና በመጨፈር የክረምቱን መፈጸም እና የአዲስ ዓመት መቃረብን በድምቀት አጠናቅቀው ወደየ ቤታቸው ይመለሳሉ ነው ያለችው። ይህን የነፃነት በዓል በድምቀት ለማክበር በጉጉት እየተጠባበቀች መኾኑንም ትገልጻለች።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች ቡድን መሪ ዘመናይ ዳምጤ እንግጫ ነቀላ በጎጃም የመተጫጨት ባሕል መሠረት የሚጣልበት ነው ብለዋል። በተለይም ወንዶች የክንፈር ወዳጅ ያበጃሉ። በዚህም ልጃ ገርዶች አምረው እና ተውበው አሸብርቀው ወደ እንግጫ መንቀያ ቦታ እንደሚሄዱ ገልጻለች። በለተይም የበዓሉ ዋዜማ ጳጉሜን ወር ሴቶች ፀጉራቸውን ይሠራሉ፣ ከወገባቸው ምሪ ያስራሉ፤ ወንዶች ደግሞ ወንጨሬ እና እጀጠባብ ይለብሳሉ፣ ዱላም ይይዛሉ ብለዋል። ከዚያም በአጃቢነት አብረው ይሄዳሉ ነው ያሉት።
በዓሉ የልጃገረዶች የነፃት በዓል በመኾኑ በርካታ ዜማዎችን ያዜማሉ እንዲህ ሲሉ፦
አበባዬ ሻደይ፣ አበባም ያብባል፣ ከሴይም ያብባል፣
የጎጃም ሁሉ ቆንጆ ልሳም ልሳም ይላል።
በዚህ በዓል በመተጫጨት ለወግ ማዕረግ የደረሱ ሰዎች አሉ ያሉት ቡድን መሪዋ የቤተሠብ መሠረት የሚጥል ባሕላዊ ትውፊት ነው ብለዋል።
ይህ ባሕላዊ ዕሴት ድባቡ እየደበዘዘ የመጣ ቢኾንም ባሕሉን ለማስቀጠል የባሕል ቡድን በማደራጀት ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
✍️ በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚኾኑበት አሠራር ተግባራዊ እንደሚኾን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።