የ”ሚስ ሻደይ” አሸናፊዎች የዋግ ኽምራ የባሕል አምባሳደር ሊደረጉ ነው።

5
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የ”ሚስ ሻደይ” ቁንጅና ውድድር አሸናፊዎችን የብሔረሰቡ የባሕል አምባሳደር በማድረግ እና አስፈላጊውን የሞዴሊንግ ሥልጠና በመስጠት ለመደገፍ ማቀዱን አስታውቋል።
የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ በዋግ ኽምራ ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የልጃገረዶች በዓል ሲኾን የቁንጅና ውድድሩ የበዓሉ አንዱ ዋና ማድመቂያ ነው። ኾኖም ባለፉት ዓመታት ያሸነፉ ቆነጃጅት ባሕሉን ለማስተዋወቅ የመንግሥት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው የ2015 ሚስ ሻደይ አሸናፊዋ ሞዴል ማርካን ምሥጋናው ተናግራለች።
በግሏ በአዲስ አበባ እና በጎንደር በተካሄዱ ውድድሮች ዋግን ወክላ ብትወዳደርም ከባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያው አንዳችም ድጋፍ እንዳልተደረገላት ገልጻለች።
ውድድሩ ለመርሐግብር ማሟያነት ብቻ ከመካሄድ አልፎ ለዘርፉ ዕድገት የሚበጅ ለውጥ እንደሚያስፈልገውም አስተያየቷን ሰጥታለች።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ይርጋ ማርዬ ባለፉት ዓመታት ለአሸናፊዎች በቂ ድጋፍ አለመደረጉን ጠቁመዋል። ለዚህም በአሸናፊዎቹ ዘንድ የነበረው ተነሳሽነት መቀነስ እና ማኅበረሰባዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት እንደነበሩ አብራርተዋል።
አቶ ይርጋ አክለውም በዘንድሮው ውድድር አሸናፊ የምትኾነው “ሚስ ሻደይ” የሞዴሊንግ ሥልጠና እንድታገኝ፣ የተለያዩ አካባቢዎችን በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ እንድታደርግ እና በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሚሠሩ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ እንድትሳተፍ በማድረግ የዋግ ኽምራ የባሕል አምባሳደር እንደምትደረግ አስታውቀዋል።
ለዚህም ተወዳዳሪዎች ከወዲሁ በዘርፉ ለመቀጠል ከፍተኛ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመተጫጫ እና የከንፈር ወዳጅ መገናኘው እንግጫ ነቀላ
Next articleየባሩድ ጭስ ሳይኾን የብዕር ማዕዛን ለተማሪዎች መፍቀድ ግድ ይላል!