የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚኾኑበት አሠራር ተግባራዊ እንደሚኾን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

14
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲኾኑ የሚያስችለው አዲስ አሠራር ወደ ተግባር ለማስገባት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የሥራ ስምምነት ተፈራርሟል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ይህ ስምምነት የውጭ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት መብት ለማስከበር ብሎም የቤት አቅርቦትን ለማሥፋት ያለመ ነው ብለዋል።
በመመሪያ ቁጥር 1147/2018 መሠረት የሚተገበረው አሠራር የተለያዩ ተቋማት በየድርሻቸው የውጭ ዜጎችን የማጣራት፣ የመረጃ ማረጋገጥ እና የፈቃድ ሂደት እንዲያከናውኑ ያስችላል ተብሏል።
የውጭ ዜጎች ቤት ለመግዛት የጸና ፓስፖርት፣ የወንጀል ታሪክ አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ሰነድ እና ከሀገር ደኅንነት አንጻር የሚያስፈልጉ መረጃዎች ይጠየቃሉ።
በተጠቀሰው አሠራር መሠረት የቤቱ ዋጋ ከ150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በታች እንዳይኾን መስፈርት ተቀምጧል፤ የገንዘብ መስፈርቱም እንደ ከተማው ሁኔታ ሊለያይ እንደሚችል ነው የተገለጸው።
የቤት ግዢ ፈቃዱ የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ ያለው ሲኾን በአሳማኝ ምክንያት ግዢው ከዘገየ በ90 ቀናት ውስጥ ማሳወቅ እና ማራዘም እንደሚቻልም መመሪያው አስቀምጧል። አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የቤት ግዢ ፈቃድ የሚያገኘው ለአንድ ቤት ሲኾን ለሀገር ያለው ጥቅም ከፍተኛ ኾኖ ከተገኘ ተጨማሪ ፈቃድ ሊሰጠው እንደሚችል ነው የተነገረው።
📌የደኅንነት ጉዳይ
የተለያዩ የወንጀል ታሪክ ያላቸው ወይም ከሀገር ደኅንነት አንጻር አጠያያቂ የኾኑ ግለሰቦች የቤት ባለቤትነት መብት እንደማያገኙ ተገልጿል። በዚህም የፌዴራል ፖሊስ እና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት የሚኖራቸው የማጣራት ሚና ወሳኝ ነው ተብሏል።
📌የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ
አሠራሩ በቀጥታ የመሬት ባለቤትነትን አይሰጥም። የቤቱ ባለቤትነት ሲረጋገጥ ከመሬት ጋር በተያያዘ የሊዝ መብት እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በሕጉ መሠረት የሚታይ መኾኑ ተብራርቷል።
📌ቤቱን ስለመጠቀምና ስለመሸጥ ቤቱን ለንግድ ዓላማ ከመጠቀም ይልቅ ለመኖሪያነት እንዲውል መስፈርት ተቀምጧል፤ ባለቤቱም ማከራየት ይችላል። ቤቱን ለመሸጥ ሲፈልግ በውጭ ምንዛሬ የመሸጥ እና ገንዘቡን ከሀገር ውጭ የመውሰድ ጉዳይም በሕጉ እና በተያያዙ የፋይናንስ አሠራሮች መሠረት የሚፈጸም ይኾናል።
የውጭ ዜጎችን የቤት ባለቤት የማድረግ አሠራር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የከተሞችን ልማት ለማፋጠን እና የቤት አቅርቦትን ለማስፋት እንደሚያግዝ ተገልጸዋል።
በሌላ በኩል የውጭ ዜጎች የቤት ባለቤት መኾን በንብረት ዋጋ፣ በየከተሞች የመሬት አጠቃቀም፣ በውጭ ምንዛሬ ፍሰት እና በሀገር ደኅንነት ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ተጽዕኖ በተገቢው መከታተል ይጠይቃል። በተለይም የፋይናንስ መረጃ ማጣራት፣ የገንዘብ ምንጭን ማረጋገጥ እና የተከለከሉ ግለሰቦች ወይም አካላት ከሂደቱ ውጭ መኾናቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ ይኾናል።
በአጠቃላይ አዲሱ አሠራር የውጭ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ የታለመ ሲኾን ዋናው ፈተና የኢንቨስትመንት ጥቅምን ከሀገር ጥቅም፣ ከዜጎች የቤት ፍላጎት እና ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በሚመጣጠን መልኩ መተግበር ይኾናል ተብሏል።
✍️ ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአልማ በትምህርት ቤቶች ልማት ላይ ውጤታማ ሥራ እየሠራ ነው።