
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የደቡብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ትምህርት ቤቶችን የማደስ፣ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችን የመገንባት እና የማስተማሪያ ግብዓቶችን የማሟላት ሰፊ ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውቋል።
በተከናወኑት የልማት ሥራዎች ላይ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሀብቶች እና ነጋዴዎች የተሳተፉበት የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የደቡብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ወርቁ መረሻ እንደገለጹት በተከናወኑት ተግባራት ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
በቀጣይም የዲጂታል ትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ጨምሮ ሁለገብ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ለተመዘገበው ውጤት ዕውቅና በመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ የተገነቡት ጥራታቸውን የጠበቁ ክፍሎች ለትምህርት ጥራት ማደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን አልማ ለሚያደርገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ከማኅበሩ ጎን በመኾን ልማቶችን ለማፋጠን ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
